ወደ መጨረሻው ምዕራፍ በደረሰው የምድብ ሀ ፉክክር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በማሸነፍ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም ለመመለስ ሲቃረብ ተከታዮቹ ቤንች ማጂ ቡና እና ወልደያ ያለ ጎል ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። ዱራሜ ከተማም መውረዱን አረጋግጧል።
የምድብ ሀ የ24ኛ ሳምንት የመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄድ ቀዳሚ የነበረው የአዲስ ከተማ እና የንግድ ባንክ ጨዋታ ንግድ ባንክን አሸናፊ አድርጓል። በመጀመርያው አጋማሽ ብልጫ ወስደው የተጫወቱት አዲስ ከተማዎች በርከት ያሉ የጎል እድሎችን ከመፍጠራቸው ባሻገር የንግድ ባንክን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ችለው ነበር።
በተለይ በአጥቂያቸው ከተማ ገረመው አማካኝነት በጥሩ ሁኔታ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የወጣው የሚያስቆጭ ሆኖ ሲያልፍ በአዲስ ከተማዎች በኩል ኳሱ የጎል መስመሩን አልፎ ከውስጥ ነው የወጣው ጎሉ መፅደቅ ነበረበት በማለት ጥያቄ አንስተዋል። በሌላ አጋጣሚ ወጣቱ አጥቂ አሸናፊ በቀለ ከመስመር የተላከለትን ኳስ አገባው ሲባል ወደ ላይ የሰደዳት ኳስ የአዲስ ከተማዎች ተጠቃሽ የጎል እድል ነበር።
በሁለተኛው አጋማሽ አሁንም አዲስ ከተማዎች መልካም እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን በመቀጠል አጥቂው ሰለሞን ጌዲዮን መሬት ለመሬት መቶት ግብጠባቂው እንደምንም ያወጣው በጨዋታው ጎል ለማግኘት ያደረጉት ሌላ ማሳያ ነው። የቡድናቸውን ክፍተት ለማረም ከ65ኛው ደቂቃ በኋላ የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ ያደረጉት አሰልጣኝ በፀሎት ከቅያሪው በኋላ እንቅስቃሴያቸው ተሻሽሎ ደጋግመው ወደ ጎል መድረስ ጀምረዋል። የግራ መስመር ተከላካዩ ኪሩቤል ወንድሙ ከቅጣት ምት መትቶ ግብጠባቂው ያወጣው እና አቤል ሀብታሙ በግንባሩ ገጭቶ የግቡ አግዳሚ የመለሰው ንግድ ባንኮች በጨዋታው የፈጠሩት ግልፅ የማግባት አጋጣሚ ሆኖ አልፏል።
የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ወደ መጠናቀቂያ ደርሶ ያለ ጎል ይጠናቀቃል ሲባል በ88ኛው ደቂቃ ኪሩቤል ወንድሙ ከግራ መስመር በጥሩ መንገድ ያሻገረውን ተቀይሮ የገባው ሀይከን ዳውሮ በግንባሩ ገጭቶ ወሳኙን የማሸነፊያ ጎል ለንግድ ባንክ አስቆጥሮ ጨዋታው አንድ ለምንም ተጠናቋል።
በዕለቱ በተካሄደው ሁለተኛ መርሐ ግብር የዱራሜ ከተማ እና ባቱ ከተማ ጨዋታ በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ከበድ ባለ ዝናብ ታጅቦ እምብዛም ሳቢ ያልነበረ እንቅስቃሴ ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ቀዳሚ የነበሩት ዱራሜ ከተማዎች ነበሩ። በ39ኛው ደቂቃ ከርቀት የተመታውን ጠንካራ ኳስ ግብጠባቂው ሲተፋው ካፉ ካስትሮ አግኝቶ ወደ ጎልነት ቀይሮታል።
ከዕረፍት መልስ ባቱዎች በጨዋታው ተፅኗቸው ከፍ ብሎ በተደጋጋሚ የዱራሜን የግብ ክልልን መፈተሻቸውን አጠናክው በመቀጠል በ78ኛው ደቂቃ ወጣቱ አጥቂ ዮሐንስ ደረጄ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለዋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ባቱዎች ቅያሪዎችን በማድረግ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ ቢንቀሳቀሱም ጨዋታው በአንድ አቻ ውጤት ተጠናቋል።
ዱራሜ ከተማ ጨዋታውን በአቻ ውጤት መውጣቱን ተከትሎ ሁለት ጨዋታ እየቀረው በመጣበት ዓመት ዳግም ወደ አንደኛ ሊግ ለመውረድ ተገዷል።
የዕለቱ የመጨረሻ እና ተጠባቂ ጨዋታ የነበረው ቤንች ማጂ ቡና ከወልድያ ያለ ጎል ተጠናቋል።
በጠንካራ ፉክክር ከአዝኝ እንቅስቃሴ ጋር ሲያስመለክተን በነበረው በዚህ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ወልድያዎች በበድሩ ኑርሁሴን እና ቢንያም ጾመልሳን አማካኝነት ግልፅ የማግባት ዕድሎችን ቢፈጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ቤንች ማጂ ቡናዎች ከወትሮው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በተወሰነ መልኩ ቢቀዛቀዝም አልፎ አልፎ በዘላለም እና እሱባለው አማካኝነት ጎል ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በሁለተኛው አጋማሽ በሙሉ አቅማቸው ማጥቃት ውስጥ የገቡት ቤንች ማጂ ቡናዎች ጥረታቸው በወልድያ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀትን ሰብሮ ለመግባት ሲቸገሩ ታይተዋል። በመጨረሻው ደቂቃዎች ወልድያዎች በሁለት አጋጣሚ እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራዎች ቢያደርጉም የዕለቱ ኮከብ ግብጠበቂ መስፍን ቤንች ማጂ ቡናን ከመሸነፍ ታድጎ ጨዋታው ያለ ጎል ተጠናቋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ያለ ጎል በመጠናቀቁን ተከትሎ የምድቡ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀሪው ሁለት ጨዋታ ውስጥ አንድ ነጥብ የሚያሳካ ከሆነ ከአምስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ የሚመለስ መሆኑን ያረጋግጣል።