መረጃዎች | 98ኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ፋሲል ከነማ

በ 23 ነጥቦች እና 11 ደረጃዎች ተበላልጠው 16ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ለገጣፎ ለገዳዲ እና ፋሲል ከነማ በወራጅ ቀጠናው ነፍስ ለመዝራት እና ወደ መሪዎቹ ለመጠጋት ጥሩ ፉክክር እንደሚያደርጉበት የሚጠበቀው ጨዋታ ቀን 9 ሰዓት ላይ ይጀመራል።

ባለፈው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ድንቅ እንቅስቃሴ በማድረግ 2ለ0 መምራት ችለው የነበሩት ለገጣፎዎች በሁለተኛው አጋማሽ በተቆጠሩባቸው ሦስት ግቦች ምክንያት ግን አንድም ነጥብ ሳያሳኩ መቅረታቸው ይታወሳል። ሆኖም በተደጋጋሚ እያሳዩት የመጡት ጠንካራ እንቅስቃሴ ለመትረፍ ተስፋ ባጡበት ሰዓት መምጣቱ እጅግ የሚያስቆጫው ነው። በሂሳባዊ ስሌት አሁንም ቢሆን መውረዱን ያላረጋገጠው ቡድኑ የሌሎቹን ቡድኖች ውጤት ለመጠበቅ የሚገደድ ቢሆንም በእጁ ያሉት ጨዋታዎች ላይ ድል ተቀዳጅቶ ያለውን ዕድል ለመሞከር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል።

\"\"

ከተከታታይ ድሎች በኋላ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ዐፄዎቹ ወጥ ያልሆነው አቋማቸው ከሊጉ መሪ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት 17 አድርሶታል። ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች በጨዋታ ካስቆጠሯቸው ሰባት ግቦች ስድስት (85.71%) የሚሆኑትን ግቦች በሁለተኛው አጋማሽ ያስቆጠረው ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ የሚኖረው ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር መቻኮል ውስጥ እየከተቱት ይገኛሉ። ከተጠበቁበት ውጤት አንጻር ተዳክመው የቀረቡት ፋሲሎች በአዲሱ አሰልጣኛቸው ስር መጠነኛ መነቃቃት ቢያሳዩም አሁንም ቢሆን ተከታታይ ድሎችን ለማስመዝገብ በተጠቀሰው አጋማሽ ግቦችን ማስቆጠር እና ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ መቆጣጠር ይገባቸዋል።

በለገጣፎ በኩል በረከት ተሰማ እና  ሱለይማን ትራኦሬ በጉዳት ሱራፌል አወል ደግሞ በቅጣት ጨዋታው የሚያመልጣቸው ሲሆን ጋናዊው ግብ ጠባቂ ኮፊ ሜንሳህ ከስድስት ጨዋታ ቅጣቱ ይመለሳል። በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ የናትናኤል ገብረጊዮርጊስ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በፕሪሚየር ሊጉ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገናኙበት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ፋሲል ከነማ 3-0 መርታት ችሏል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

የምሽቱ መርሐግብር በ 30 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ድሬዳዋ ከተማዎች በ 41 ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች ሲያገናኝ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ እና ከመሪዎቹ ለመጠጋት የሚደረገው ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በደረጃ ሰንጠረዡ ሜዳልያ ደረጃ ውስጥ ካሉት ቡድኖች ውጪ ከፍተኛውን የግብ መጠን (33) ያስቆጠሩት ብርቱካናማዎቹ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ከፍተኛ ፉክክር ገጥሟቸው በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች ጨዋታውን በመርታት ጣፋጭ ድል ተጎናፅፈው ከተከታታይ ሁለት ሽንፈቶች አገግመዋል። በተለይም የግብ ጠባቂያቸው ዳንኤል ተሾመ ብቃት እና ተከላካዮቹ የተጋጣሚን ቡድን ተጫዋቾች ከጨዋታ ውጪ ወደ ሆነ አቋቋም ሲያስገቡበት የነበረው መንገድ የሚደነቅ ነበር። ሆኖም በክፍተቶቹ ልክ ብዙ ጠንካራ ጎኖች ያሉት ቡድኑ በተሻለ መነሳሳት ለነገው ጨዋታ ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"

ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ በመርታት ሁለት ጊዜ አቻ ወጥተው በሁለቱ የተሸነፉት ኢትዮጵያ መድኖች ማግኘት ከሚገባቸው 15 ነጥብ 5ቱን ብቻ ማሳካታቸው ከሊጉ መሪ ቅዱስ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ 10 ነጥቦች ርቀት ላይ እንዲቀመጡ ምክንያት ሆኖባቸዋል። በጊዜያዊነት ውጤቱ እንዳይፀድቅበት በተወሰነው የሲዳማ ቡና ጨዋታም ቡድኑ ተዳክሞ የቀረበበት መንገድ በዋንጫ ግስጋሴው ላይ ዕክል እንደሚፈጥርበት የሚጠበቅ በመሆኑ በቶሎ ሊቀረፍ ይገባዋል። ከጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ዕኩል ከፍተኛውን የግብ መጠን (43) ያስቆጠሩት ኢትዮጵያ መድኖች ባለፉት ስምንት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ማስተናገዳቸው ደግሞ በቡድናቸው ውጤታማነት ላይ ውሃ የሚቸልስ ነው። ሆኖም በነገው ዕለት ሜዳ ውስጥ በቅጣት ምክንያት በማይገኙት አሰልጣኙ ገብረመድኅን ኃይሌ የማይመሩት መድኖች በተለይም ይህንን የኋላ መስመራቸውን በማጠናከር ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ከሚገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች ሙሉ ነጥብ ለመውሰድ ብርቱ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ኢትዮጵያ መድን ነገ ከዋና አሰልጣኙ በተጨማሪ በመጨረሻው ጨዋታ በቀይ ካርድ ያጣው ኪቲካ ጀማን የማይጠቀም ሲሆን በድሬዳዋ ከተማ በኩል ያሲን ጀማል እና ያሬድ ታደሰ በጉዳት ምክንያት ከጨዋታው ውጪ ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ 3-1 መርታቱ ይታወሳል።