አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ዕግድ ተላለፈባቸው

የኢትዮጵያ መድን እና ሲዳማ ቡና ውጤት ሲፀድቅ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ከበድ ያለ ቅጣት አስተናግደዋል። 

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ እሁድ ሚያዝያ 29 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማስተላለፉ ይታወቃል። በወቅቱ በፕሪምየር ሊጉ አ.ማ. የተቋቋመው ቴክኒካል ኮሚቴ የ23ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ አንዱ በሆነው የኢትዮጵያ መድንና ሲዳማ ቡና ግጥሚያ ዙሪያ ምርመራ እያደረገበት በመሆኑ የኮሚቴው የቅድመ ምርመራ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ የጨዋታው ውጤት እንዳይጸድቅ እና ከጨዋታው ጋር የተያያዙ የዲሲፕሊን ውሳኔዎች እንዲታዩ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል። በመሆኑም የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ክለቦቹ ቀጣይ ጨዋታዎችን ከመጫወታቸው ቀድም ብሎ ውጤት እና የዲሲፕሊን ውሳኔዎች ዛሬ ይፋ አድርጓል።
\"\"

በተጫዋችና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች ሁለት ተጫዋቾችና አንድ አሰልጣኝ ላይ ቅጣት ተላልፏል። በዚህም የኢትዮጵያ መድኑ ኪቲካ ጅማ እና የሲዳማ ቡናው ሙሉቀን አዲሱ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያሰጥ ጥፋት በመፈፀማቸው ቀይ ካርድ አይተው ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ ለፈፀሙት ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱ እንዲሁም የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ክለባቸው ከ ሲዳማ ቡና ጋር ባደረገው ጨዋታ ዳኛን አፀያፊ ስድብ በመሳድብ ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ የቡድን አመራሩ ለፈፀሙት ጥፋት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ የውድድር ደንብ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 10000 /አስር ሺ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል።
\"\"
በተጨማሪም አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ 23ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ ግጥሚያው ከተጠናቀቀ በኋላ ለሱፐር ስፖርት በሰጡት የድህረ ጨዋታ ቃለመጠይቅ ወቅት የዕለቱን የጨዋታ አመራሮች አሰራራቸውን ያለአግባብ የተቸና ስሜታቸውን የጎዳ አሰተያየት ስለመስጠታቸው ሪፖርት የቀረበባቸው በመሆኑ አሰልጣኙ ለፈፀሙት ጥፋት ከተላለፈባቸው ቅጣት በተጨማሪ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 /ሶስት ወር/ እንዲታገዱና ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 10000 /አስር ሺህ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል።