ሪፖርት | የሱራፌል ሁለት ግሩም ግቦች ዐፄዎቹን ለድል አብቅተዋል

ዐፄዎቹ ለገጣፎ ለገዳዲን 2-0 በማሸነፍ ደረጃቸውን አሻሽለዋል።

ፋሲል ከነማ የተገቢነት ክስ አስገብቶ በጀመረው ጨዋታ ለገጣፎዎች በወልቂጤ ከተሸነፈው ስብስብ በሽር ደሊል ፣ በረከት ተሰማ እና ሱራፌል ዐወልን በኮፊ ሜንሳህ ፣ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ እና ኤልያስ አታሮ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል። ዐፄዎቹ በበኩላቸው ከአርባምንጭ ከተጫወተው ቀዳሚ አሰላለፍ ሽመክት ጉግሳ ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ሀብታሙ ገዛኸኝ በሱራፌል ዳኛቸው ፣ በዛብህ መለዮ እና አምሳሉ ጥላሁን ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

በሁሉም ረገድ ተመጣጣኝ የነበረው የመጀመርያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት ፍላጎት ያሳዩበት ነበር። በሙከራ ረገድም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች የተፈጠሩበት ነበር። በፋሲል ከነማ በኩል በጨዋታው የተሻለ የማጥቃት ነፃነት የነበረው መናፍ አወል በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ቡድኑን መሪ ለማድረግ ተቃርበው ነበር ፤ በተለይም ተከላካዩ ከዓለምብርሀን የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ መቶት ግብ ጠባቂው እንደምንም የመለሰው ኳስ ለግብ የቀረበ ነበር። መናፍ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ናትናኤል በግንባር ያደረገው ሙከራም ሌላ ሙከራ የሚጠቀስ ነው።

በአጋማሹ የመጀመርያ ደቂቃዎች ኳስ በመቆጣጠር የኋላ ኋላ ደግሞ በጥሩ የመከላከል ቅርፅ የተጋጣሚን አጨዋወት ለማክሸፍ የተጫወቱት ለገጣፎዎች በአጋማሹ ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ካርሎስ ዳምጠው ከቅጣት ምት በቀጥታ መቶት ቋሚው የመለሰበት ሙከራ እጅግ ለግብ የቀረበ ነበር።

በአጋማሹ መጨረሻ ደቂቃም የአጋማሹ ትልቁ የጎል ሙከራ ተፈጥሯል። ለገጣፎዎች በአማኑኤል፣ ሙሉጌታ እና መሐመድ አማካኝነት በፈጠን መልሶ ማጥቃት ወደ ሳጥን ይዘውት የገቡት ኳስ መሐመድ ለተፈራ በግሩም መንገድ ቢያቀብለውም ተጫዋቹ ከግቡ አቅራብያ ሆኖ ዕድሉን አምክኖታል። የፋሲሉ ግብ ጠባቂ ሳማኪ ሙከራውን ያከሸፈበት መንገድም የሚደነቅ ነበር። ፋሲሎች ግን እንቅስቃሴው በቀጠለበት ደቂቃ በሱራፌል አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። አማካዩ በዛብህ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በጥሩ መንገድ ካበረደ በኋላ አክርሮ በመምታት ግሩም ግብ አስቆጥሯል። አስራ አራት የግብ ሙከራዎች የታዩበት የመጀመርያው አጋማሽም በዐፄዎቹ መሪነት መጠናቀቅ ችሏል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ጥቂት ሙከራዎች የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች የአጨዋወት ለውጥ አልታየበትም ሆኖም ፋሲል ከነማዎች በማጥቃቱ ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል። ካደረጓቸው ሙከራዎችም ሱራፌል ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ፤ ሽመክት ጉግሳ በተጋጣሚ ሳጥን ከማውሊ የተቀበለውን ኳስ መትቶ ወደ ውጭ የወጣው ኳስ እና ናትናኤል አክርሮ በመምታት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

በሁለተኛው አጋማሽ የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ያልቻሉት ለገጣፎዎች በአጋማሹ አንድ ለግብ የቀረበ የጠራ ዕድል ብቻ ነበር የፈጠሩት። እንደ መጀመርያው ግብ በተመሳሳይ አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ሱራፌል ሁለተኛ ግቡን አስቆጥሮ የዐፄዎቹ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። አማካዩ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ነበር ግሩም ግብ ያስቆጠረው።

ከጨዋታው በኋላ አስተያየቸው የሰጡት አሸናፊ በቀለ ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ ባለመሄዱ ፈጣን የአጨዋወት ለውጥ ለማድረግ መወሰናቸውን ገልፀው ማሸነፋቸውን እንዳለ ሆኖ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ግን አልሸሸጉም። አሰልጣኙ ጨምረውም የሱራፌል ብቃት አድንቀው እስከ ውድድሩ ፍፃሜ ድረስ ደረጃ ይዘው ለማጠናቀቅ እንደሚፋለሙ ተናግረዋል። የለገጣፎው አሰልጣኝ ዘማርያም በበኩላቸው በጨዋታው የተሻለ መንቀሳቀሳቸው እና ኳሱን ለመቆጣጠር መሞከራቸውን ገልፀው ተጋጣምያቸው ሁለት ዕድል ፈጥሮ ሁለቱም እንዳስቆጠረባቸው ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ግብ ጠባቂው ዝግጁ እንዳልነበር እና በቀላሉ ግቦች እንዳስተናገደ ጠቅሰው የመከላከል ድክመታቸውን ስር የሰደደ መሆኑ ተናግረዋል።

\"\"