በ23ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ጎልተው የወጡ ተጨዋቾች እና አሰልጣኝን የመረጥንበት ምርጥ ቡድን የሲዳማ ቡና እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ሳይፀድቅ በይደር በመቆየቱ ምክንያት በተለመደው ጊዜ ሳንገልፅ የቆየን ሲሆን አሁን ላይ ሙሉ የጨዋታ ሳምንቱ ውጤቶች በመፅደቃቸው እንደሚከተለው አሰናድተናል።
አሰላለፍ 4-1-3-2
ግብ ጠባቂ
ዳንኤል ተሾመ – ድሬዳዋ ከተማ
ድሬዳዋ ከተማ ኤሌክትሪክን በመጨረሻ ደቂቃ ጎሎች በረታበት ጨዋታ ቀድሞ ግብ ሊያስተናግድ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ተፈጥረው ነበር። ሆኖም የዳንኤል የጊዜ አጠባበቅ እና በተለይም በሁለት አጋጣሚዎች አደገኛ ኳሶችን ያዳነበት አኳኋን ቡድኑ ሳይቆጠርበት እስከማሸነፊያ ግቦቹ እንዲዘልቅ አግዞታል።
ተከላካዮች
ደግፌ ዓለሙ – ሲዳማ ቡና
ሲዳማ ቡናን ተከታታይ ድል ወሳኝ ከነበሩ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ከቡድኑ ወጣት ቡድን የተገኘው ደግፌ ተጠቃሹ ነው። በሳምንቱ ሲዳማ ቡና በመድን ላይ ድልን ሲቀናጅ ከተሰጠው የመከላከል ሚናው በይበልጥ ወደ ፊት እየተሳበም የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ያደርግ ከነበረው ብርቱ የሆነ ትጋት አንፃር በምርጥነት አካተዋል።
ምንተስኖት አዳነ – መቻል
መቻሎች የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ሲረቱ በተለይም ከኳስ ውጪ የነበራቸው ታክቲካል ዲሲፕሊን የሚያስደንቅ ነበር። የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተመችቶት እንዳይንቀሳቀስ በማድረጉ እና ክፍት ቦታዎችን በመዝጋት የፈረሰኞቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ በመመከቱ በኩል የተሳካ ቀን ያሳለፈውን የመሃል ተከላካዩ ምንተስኖት አዳነ የሳምንቱ ቡድናችን ውስጥ አካተነዋል።
ጊት ጋትኩት – ሲዳማ ቡና
ካለፈው ዓመት ብቃቱ አንፃር ዘንድሮ ተቀዛቅዞ የቆየው ጊት ሲዳማዎች ላለመውረድ በሚያደርጉት ጥረት ወሳኝ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።
ቡድኑ መድንን ባሸነፈበት ጨዋታም በተሻሻለው የሲዳማ የተከላካይ ክፍል ጥሩ ብቃት በማሳየት በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ተካቷል።
ፍራኦል መንግሥቱ – ባህር ዳር ከተማ
ፍራኦል የጣና ሞገዶቹ ከዚህ በፊት ይቸገሩበት የነበረውን ቦታ በአግባቡ ከመሸፈኑ በተጨማሪም በቡድኑ የማጥቃት ሽግግር ወቅት የሚሰጠው ፈጣን ምላሽና ወደ ሳጥን የሚልካቸው ስኬታማ የሆኑ ኳሶቹ ጥሩ የውድድር ዓመት እንዲያሳልፍ ምክንያትሆነዋል። ተጫዋቹ በዚህ የጨዋታ ሳምንትም ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን 3ለ1 ሲረታ ያሳየው እንቅስቃሴ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ አድርጎታል።
አማካዮች
ተስፋዬ አለባቸው – መቻል
መቻል ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ሦስት ነጥብን ሲያሳካ የአማካይ ተከላካዩ አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነበር። የቡድኑን ሚዛን ከመጠበቅ አልፎ በመሪነት በመታተር በማጥቃቱ እና በመከላከሉ ረገድ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋቾች ፈተና ሆኖ የዋለው ግዙፉ ተጫዋች በሳምንቱ የምርጥ ስብስባችን አካል አድርገነዋል።
አለልኝ አዘነ – ባህር ዳር ከተማ
በየሳምንቱ በሚያሳየው ድንቅ ብቃት የጣና ሞገዶቹ ደጀን መሆኑን እያስመሰከረ የመጣው አለልኝ ቡድኑን አሸናፊ እያደረጉ ያሉት የሚያስቆጥራቸው ግቦችም የብዙዎቹ ዐይን እንዲያርፉበት ምክንያት ሆነዋል። በጨዋታ ሣምንቱም ባህርዳር ከተማ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ድል ሲቀዳጅ ባሳየው ብቃት የምርጥ ቡድናችን ውሰጥ ተካቷል።
የአብሥራ ተስፋዬ – ባህር ዳር ከተማ
የጣና ሞገዶቹ ኢትዮጵያ ቡናን 3-1 ሲረቱ እንደ ቡድን አጋሩ አለልኝ አዘነ ሁሉ የተሳካ ቀን ያሳለፈው አማካዩ ወደ ቋሚነት ከተመለሰ በኋላ በቦታው የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል። በጨዋታ ሳምንቱም የፈጠራቸው በርካታ የግብ ዕድሎች ወደ ውጤት የሚቀይራቸው ቢያጡም ያሳየው የግል ብቃት ግን አድናቆትን ያተረፈ ነበር።
ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ
ፋሲል ከነማ በአርባምንጭ ከተማ ሲመራ በነበረበት ጨዋታ ቡድኑ ነፍስ ዘርቶ ከጨዋታው አንድ ነጥብን ሲያሳካ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሚና ጉልህ የሆነ ድርሻ ነበረው። ከተሰጠው የመሐል እንቅስቃሴ በተጨማሪነት ወደ መስመር በማጋደል ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ከርቀት እና ከቆመ ኳስ ያደርግ የነበረው ሱራፌል በዛብህ በጨዋታው ከመረብ ላገናኛት የአቻነት ጎል መነሻ መሆን ችሏል።
አጥቂዎች
ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ
ወልቂጤዎች ከመመራት ተነስተው ያሸነፉት ጨዋታ ያለጌታነህ ከበደ አስተዋዖ አይታሰብም ነበር። በጨዋታው በሦስቱም ግቦች ተሳትፎ የነበረው አምበሉ ሁለት ለግብ የሆኑ ኳሶች አመቻችቶ ከማቀበል ባለፈ ቡድኑን ለጣፋጩ ድል በመምራት ያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ ነበር።
ፊልፕ አጃህ – ሲዳማ ቡና
አጃህ በተከታታይ ጨዋታዎች ቡድኑን ታድጓል ፤ ቡድኑ ላለመውረድ በሚያደርገው ጥረት ወሳኝ የሆኑ ግቦች እያስቆጠረ የሚገኘው ይህ አጥቂ ከኢትዮጵያ መድን ጋር በነበረው ጨዋታ ያደረገው አመርቂ እንቅስቃሴ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን እንዲካተት አስችሎታል።
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ
የጣና ሞገዶቹ ፈቀቅ ብለው ከነበሩበት የዋንጫ ፉክክር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የነበራቸውን ልዩነት ወደ አራት የቀነሱበትን የጨዋታ ሳምንት አሳልፈዋል። ይህንን ለማድረግም ጠንካራ የነበረውን የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ በድል መደምደም ከቡድኑ ይጠበቅ የነበረ ሲሆን ፈተናውን ከጥሩ እንቅስቃሴ ጋር መውጣቱ የቡድኑን አሰልጣኝ ኮከብ አድርገን እንድንመርጥ መነሻ ሆኖናል።
ተጠባባቂዎች
ውበሸት ጭላሎ
መሳይ ጳውሎስ
ያሬድ ባየህ
ሙሉቀን አዲሱ
ከነዓን ማርክነህ
ሀብታሙ ታደሰ
ኢብሳ በፍቃዱ
ቢኒያም ጌታቸው