መረጃዎች | 91ኛ የጨዋታ ቀን

የሊጉ 24ኛ ሳምንት ማሳረጊያ በሆኑት ሁለት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አሰናድተናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ

09:00 ላይ የሚጀምረው ጨዋታ ከሽንፈት የሚመለሰው የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስን ድል እና ጎል ከራቁት ሀዋሳ ከተማ ያገናኛል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታዩ ባህር ዳር ከተማ ቀደም ብሎ ጨዋታውን በማድረጉ ይመራበት የነበረው የነጥብ ርቀት ወደ አንድ ዝቅ ብሏል። ቡድኑ ከተከታታይ ድሎች በኋላ በመቻል ያስተናገደው ሽንፈት ልዩነቱ ለመጥበቡ ዋነኛ ምክንያት ነበር። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሽንፈቱ ባሻገር ከኳስ ቁጥጥር ባለፈ በሚታወቅበት አኳኋን በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ክፍተቶችን ፈልጎ በማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን የሚያደርግበት እንቅስቃሴም አብሮት አልነበረም። በመሆኑም ቡድኑ ነገ በተለይም በመጨረሻው የሜዳ ክፍል ያለውን አፈፃፀም አሻሽሎ ለመቅረብ እንደሚሞክር ይጠበቃል።

\"\"

ሀዋሳ ከተማ ከድል ጋር ከተራራቀ አራት ጨዋታዎች አልፈውታል። በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ተመሳሳይ የ1-0 ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ በመጨረሻ ጨዋታው ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ያለ ግብ ተለያይቶ አንድ ነጥብ አሳክቷል። ሀዋሳዎች በመቀመጫ ከተማቸው የሊጉን መሪ መርታት የሚሰጣቸው አዕምሯዊ ከፍታ እንዳለ ሆኖ በደረጃ ሰንጠረዡ ተንሸራተው ከወገብ ላይ ካሉበት እስከ አራተኛነት ከፍ ማለትም ያስችላቸዋል። ይህንን ለማድረግ ግን ወልቂጤ ከተማ ላይ ሦስት ግቦችን ካስቆጠሩ ወዲህ ለአራት ዘጠና ደቂቃዎች ኳስ እና መረብን ማገናኘት እንዳይችሉ ያረጋቸውን ደካማ ጎን ፈልገው ማግኘት ዋነኛ የቤት ስራቸው ይሆናል።

በነገው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ሙጂብ ቃሲም ፣ ብርሀኑ አሻሞ እና ወንድማገኝ ኃይሉን በጉዳት ምክንያት የሚያጣ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጋቶች ፓኖም ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል ፣ ምኞት ደበበ እና ሱለይማን ሀሚድ ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

ሁለቱ ቡድኖች ነገ ለ46ኛ ጊዜ ይገናኛሉ። በእስካሁኖቹ ጨዋታዎቻቸው 80 ግቦችን ያስቆጠሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 28 ጊዜ ባለድል ሲሆኑ 34 ግቦች ያሏቸው ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ሰባት ጊዜ አሸንፈዋል።

ሲዳማ ቡና ከ መቻል

ያሳለፍነውን የጨዋታ ሳምንት ወሳኝ በነበሩ ተመሳሳይ የ1-0 ድሎች ያለፉት እና ሁለት ተካታታይ ጨዋታዎችን ያሸነፉት ሲዳማ ቡና እና መቻል የ24ኛ ሳምንቱን የመጨረሻ ጨዋታ ያደርጋሉ።

ሲዳማ ቡና ወደ መቀመጫ ከተማው ተመልሶ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦችን ማሳካቱ ከአስከፊው የውድድር ዘመን ለማገገም ትልቅ እርምጃ ሆኖለታል። ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ ይቀመጥ እንጂ ነገ ድል ከቀናው ነጥቡን 30 በማድረስ የተሻለ እፎይታን ማግኘት ይችላል። ሁለቱ ድሎች በ1-0 ጠባብ ውጤቶች እንደመገኘታቸው እና በፊልፕ አጃህ ብቻ የተቆጠሩ መሆናቸው ቡድኑ አሁንም የማጥቃት አማራጩን ማስፋት እንደሚያስፈልገው ይጠቁማል። ይህንን ለማድረግም ከበፊቱ የተሻለ ጫናው ቀለል ያለለት በመሆኑ በነገው ጨዋታ የማጥቃት አጨዋወቱን አሻሽሎ እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

ከወላይታ ድቻው ሽንፈት በኋላ በድሬዳዋ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ድልን ያሳኩት መቻሎች ወደ 32 ነጥብ ከፍ ብለዋል። በዚህም ከአደጋው ዞን ርቀው በሰንጠረዡ አጋማሽ መቀመጥ ሲችሉ የነገው ጨዋታ ደግሞ እስከ አራተኛ ደረጃ ከፍ ሊያደርጋቸው ይችላል። በመከላከሉ ረገድ በተለይም በቅዱስ ጊዮርጉሱ ጨዋታ እንደታየው ከሆነ ቡድኑ የሚያስተናግደውን የሙከራ ብዛት በመቀነስ እና የተጋጣሚን ቁልፍ ተጫዋቾች በመቆጣጠሩ ረገድ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ለነገም ይህን በጎ ጎን በፊት መስመሩ የተሻለ የአፈፃፀም ብቃት ማጀብ የቡድኑ ዋና ትኩረት ይመስላል።

\"\"

በጨዋታው የሲዳማ ቡናዎቹ ሙሉቀን አዲሱ በቅጣት ቴዎድሮስ ታፈሰ ደግሞ በጉዳት በነገው ጨዋታ ቡድናቸውን አያገለግሉም። በተጨማሪም ሙሉዓለም መስፍን እና ሳላሀዲን ሰይድ ወደ ልምምድ ቢመለሱም መሰለፋቸው አጠራጥሯል። በሌላ በኩል ከቡድኑ ጋር ያልነበረው አበባየው ዮሐንስ በበኩሉ ወደ ስብስቡ ተመልሷል። በመቻል በኩል ደግሞ ዳግም ተፈራ እና ፍፁም ዓለሙ ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን በ23 ጨዋታዎች የተገናኙት ሲሆን 47 ጎሎችን አስቆጥረዋል። ሲዳማ ቡና ስምንት መቻል ደግሞ ሰባት ድሎችን አሳክተው ስምንት ጊዜ አቻ ሲለያዩ መቻል 23 ሲዳማ ደግሞ 24 ግቦችን አስመዝግበዋል።