ሪፖርት | ሲዳማ ቡናዎች ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ በፊሊፕ አጃህ ብቸኛ ግብ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በተደረገው የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ሲዳማ ቡና መቻልን በፊሊፕ አጃህ ግብ 1-0 በመርታት ደረጃውን አሻሽሏል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ሲዳማ ቡና እና መቻልን ሲያገናኝ ሲዳማዎች በ 23ኛው ሳምንት መድንን 1-0 ከረቱበት አሰላለፍ አበባየሁ ዮሐንስን በሙሉቀን አዲሱ ተክተው በማስገባት ሲጀምሩ መቻሎች በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስን 1-0 ሲረቱ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ቀርበዋል።

\"\"

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ጥሩ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ብልጫውን መውሰድ የቻሉት ሲዳማዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ወደ ሳጥን በላከው እና ግብ ጠባቂው ውብሸት ጭላሎ በጥሩ ንቃት ባቋረጠው ኳስ የተጋጣሚን የግብ ክልል ፈትሸው ሲመለሱ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም መቻሎች በአጋማሹ የተሻለ ሙከራቸውን አድርገዋል። በዚህም ሳሙኤል ሳሊሶ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ምንተስኖት አዳነ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።


ሲዳማ ቡናዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ሲችሉ 33ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ፍሬው ሰለሞን ከመቻሎች የተቀማውን ኳስ በረጅሙ ለይገዙ ቦጋለ አቀብሎት በግራ መስመር የነበረው ይገዙ ቦጋለም ወደ ሳጥን በግሩም ሁኔታ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ፊሊፕ አጃህ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላም ይገዙ ቦጋለ ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ውብሸት ጭላሎ ይዞበታል።


ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅቶ ለመውጣት እጅግ የተቸገሩት መቻሎች 44ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስተናገድ እጅግ ተቃርበው ምንተስኖት አዳነ አትርፏቸዋል። ፊሊፕ አጃህ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ለፍሬው ሰለሞን ሲያቀብል ፍሬው ኳሱን ወደ ግብ ለመምታት ሞክሮ ሙሉ በሙሉ ሳያገኘው በመቅረቱ ሲቆረጥበት ያንኑ ኳስ ያገኘው እንዳለ ከበደ ያደረገውን ሙከራ ተከላካዩ ምንተስኖት አዳነ ተደርቦ መልሶታል። የተመለሰው ኳስ የቀኙን ቋሚ ገጭቶ ሊገባ ሲልም ራሱ ምንተስኖት በግሩም ቅልጥፍና ከመስመሩ እንዳያልፍ አድርጎታል።

ከዕረፍት መልስ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ተሻሽለው የቀረቡት መቻሎች አጋማሹ በተጀመረ በሴኮንዶች ውስጥ ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ከዛ አጋጣሚ በኋላ ግን በኳስ ቁጥጥሩ እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩልም ብልጫውን መውሰድ ችለዋል። በተለይም 54ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ በመሆን አሻግሮት የኳሱ ኃይል ተጨምሮበት አጥቂው እስራኤል እሸቱ በሆዱ ገፍቶ በመሞከር ያባከነው ኳስ በጨዋታው የመጀመሪያው የጠራ የግብ ዕድላቸው ነበር።


በሁለተኛው አጋማሽ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ሲዳማዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ውጤት ማስጠበቁን ሲመርጡ ለግብ የቀረበ ሙከራ ለማድረግም እስከ 76ኛው ደቂቃ ለመጠበቅ ተገደዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ይገዙ ቦጋለ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ያደረገውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂው ውብሸት ጭላሎ ይዞበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም መቻሎች በተሻለ የጨዋታ ስሜት ተጭነው ቢጫወቱም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ጨዋታውም በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ሲዳማ ቡና በ 30 ነጥቦች ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የመቻሉ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንዳልነበሩ እና በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተጫዋችም ሆነ የታክቲክ ለውጥ አድርገው ለማሻሻል እንደጣሩ ሲናገሩ የመጨረሻው የሜዳ ክፍል ላይ የነበራቸው አለመረጋጋት የግብ ዕድል እንዳይፈጥሩ እንዳደረጋቸው በመጥቀስ ደረጃ ውስጥ ስለመግባት እያሰቡ መሆናቸውን እና የታችኛው ደረጃ እንደማያሳስባቸው ገልጸዋል። የሲዳማ ቡናው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በበኩላቸው የዛሬው ጨዋታ ውጤት መነቃቂያ እንደሚሆናቸው ሲገልጹ 30 ነጥብ መድረሳቸው እና ማሻሻላቸው በስነልቦና ረገድ ወሳኝ እንደሆነ ጠቁመዋል። አሰልጣኙ አክለውም በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በጣም ጥሩ እንደነበሩ እና ከዕረፍት መልስ ውጤት ለማስጠበቅ ወደኋላ ሸሽተው መጫወታቸው ስህተት እንደነበር በመጠቆም ተጫዋቾቹ ትልቅ ዋጋ እንደከፈሉ እና የፊሊፕ አጃህ ብቃትም ድንቅ እንደሆነ ተናግረዋል።