ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 24ኛ ሳምንት ምርጥ 11

እንደ ሁልጊዜው ባሳለፍነው ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ ጎልተው የወጡ ተጫዋቾችን እና አሰልጣኝ ያካተተ ቡድን ሰርተናል።

አሰላለፍ (4-4-2 ዳይመንድ)

ግብ ጠባቂ

ፔፔ ሰይዶ – ሀዲያ ሆሳዕና

በዚህ የጨዋታ ሳምንት የነጠረ ብቃት ያሳዩ ግብ ጠባቂዎች ማግኘት ባንችልም በአንጻራዊነት ግን ከወልቂጤ ከተማ ጋር ከ 75 ደቂቃዎች በላይ በጎዶሎ ተጫውተው ያለ ግብ የተለያዩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ግብ ጠባቂ የተሳካ ጊዜን አሳልፏል። ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ በተለይም በአንድ አጋጣሚ የጌታነህ ከበደን እና አቤል ነጋሽን ሙከራዎች ያመከነበት መንገድ ቡድኑ ቢያንስ አንድ ነጥብ እንዲያሳካ ያደረገ ብቃት ነበር።
\"\"
ተከላካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሰኞቹ ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ ሲለያዩ ሄኖክ አዱኛ በግሉ የተሳካ ቆይታን ማሳለፍ ችሏል። የመስመር ተከላካዩ በሀዋሳ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያን ያህል ባይፈተንም ከኳስ ጋር የነበረው ምቾት ግን ጎልቶ የታየ ነበር። ቸርነት ጉግሣ ላስቆጠረው ግብም አመቻችቶ ማቀበሉ በውጤታማነት ደረጃ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ ያደርገዋል።

ምንተስኖት አዳነ – መቻል

በሊጉ ጥሩ አቋም እያሳዩ ከሚገኙ ተከላካዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ምንተስኖት ለተከታታይ ጊዜ የቡድናችን አካል ሆኗል። መቻል በሲዳማ 1-0 ሲሸነፍ ምንተስኖት በጥቅሉ በጥሩ ንቃት ከመንቀሳቀሱ ባለፈ በአስገራሚ ሸርተቴ ከመስመር ላይ አከታትሎ ያዳናቸው እንዲሁም ተደርቦ ያወጣቸው ኳሶች ጎል ከማስቆጠር ዕኩል ትርጉም የነበራቸው ነበሩ።

በረከት ሳሙኤል – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በሳምንቱ ነጥብ ሲጋራ የተከላካዩ የሜዳ ላይ ድርሻ እና መሪነት አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነበር። የቅዱስ ጊዮርጊስን ተሻጋሪ ኳሶች ከመቆጣጠር አልፎ በአንድ ለአንድ ግንኙነት አጥቂው እስማኤል ኦሮ አጎሮ ለመፍጠር የሚሞክራቸውን የጥቃት መነሻዎች በአግባቡ ሽፋን ሲሰጥ ተመልክተነዋል።

ተካልኝ ደጀኔ – ኢትዮጵያ መድን

መድን ከድሬዳዋ ላይ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎሎችን ሲያሳካ በግራ በኩል ቡድኑ ላደረጋቸው ፈጣን ጥቃቶች ተከላካዩ የፈጠራቸው ምንጮች ቀላል አልነበሩም። ከተሰጠው የመከላከል ሚናው ባለፈ በማጥቃቱ የጎላ ሚና የነበረው የግራ እግሩ ተጫዋች ለኋላ መስመሩ ብቻ ሳይሆን ለፊት ተሰላፊዎቹ ከፈጠረው ምቹነት አንፃር የስብስባችን አካል አድርገነዋል።

አማካዮች

አማኑኤል ዮሐንስ – ኢትዮጵያ ቡና

ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮ ኤሌክትሪክን በሮቤል ተ/ሚካኤል የፍጹም ቅጣት ምት ግብ 1-0 ሲረታ ቡድኑ መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ እንዲወስድ የአማኑኤል ዮሐንስ አስተዋጽኦ የጎላ ነበር። ከኳስ ውጪም ጥሩ የነበረው አማካዩ ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ በማጥቃት ሽግግር ወቅት የፈጠራቸው የግብ ዕድሎችም በቦታው ተመራጭ አድርገውታል።

ወገኔ ገዛኸኝ – ኢትዮጵያ መድን

ኢትዮጵያ መድን ድሬዳዋ ከተማን 3ለ0 ሲረታ ወገኔ ከአማካኝ መስመር እየተነሳ ሁለት ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ከጨዋታው በኋላ የቡድኑ ምክትል አሠልጣኝ እንደገለፁት ተጫዋቹ ከተጋጣሚ ተከላካይ ጀርባ እየገባ አደጋ እዲፈጥር ኃላፊነት ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን የተጠበቀበትን ታክቲካል ድርሻ በጉዳት ምክንያት ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በሚገባ ሲወጣ አስተውለናል፡፡

ባሲሩ ዑመር – ኢትዮጵያ መድን

በየጨዋታ ሳምንቱ ወጥ ብቃት ሲያሳይ የሚታየው ባሲሩ በድሬው ጨዋታ የጎላ ሌላኛው ተጫዋች ነው፡፡ ከኳስ ጋር ምቾት ተሰምቶት የሚጫወተው አማካዩ የቡድኑን የኳስ እና የጨዋታ ቁጥጥር ከማሳደጉ በተጨማሪ ያለቀላቸው የግብ ማግባት አጋጣሚዎችንም ሲፈጥር የነበረ ሲሆን ወገኔ ያስቆጠረውን የመጀመሪያ ጎልም በጥሩ ዕይታ አመቻችቶ አቀብሏል፡፡

ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ ለገጣፎን እንዲረቱ ያስቻሉ ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው ሱራፌል የጨዋታው የትኩረት ነጥብ ነበር። አክርሮ በመምታት ኳስ እና መረብን ካገናኘባቸው ቅፅበቶች በተጨማሪ ከኳስ ጋር ራሱን ነፃ አድርጎ ተዝናኖትን በሚፈጥር አኳኋን አማካይ ክፍሉን የመራበት መንገድ ያለከልካይ የሳምንቱ ምርጥ ተጫዋች የሚያሰኘው ነበር።

\"\"

አጥቂዎች

ዱሬሳ ሹቢሳ – ባህር ዳር ከተማ

ባህርዳር ከተማ በአዳማው ጨዋታ እጅግ ተፈትኖ ሦስት ነጥብን ወደ ቋቱ ሲከት የመስመር አጥቂው የግል አቅም ለቡድኑ ድል መነሻ ነበር። በተደጋሚ የአዳማን የመስመር ሽግግር ሲረብሽ ከነበረበት አስተዋጽኦው በዘለለ ተቀይሮ ለገባው እና ብቸኛ ጎልን ላስቆጠረው አዳም አባስ ያለቀለትን አጋጣሚ የፈጠረበት መንገድ በምርጥ 11 ውስጥ ለማካተት አስችሎናል።

ብሩክ ሙሉጌታ – ኢትዮጵያ መድን

በመስመርም ሆነ በመሀል አጥቂ ቦታ ላይ መጫወት የሚችለው ብሩክ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት እጅግ መልካም የሚባል ቀን አሳልፏል፡፡ ከተሰለፈበት መስመር ከኳስ ጋርም ሆነ ያለኳስ እያጠበበ እየገባ የተጋጣሚን የተከላካይ ክፍል ሲረብሽ የነበረ ሲሆን ወገኔ ያስቆጠረውን ሁለተኛ ግብ በጥሩ ሁኔታ ከማመቻቸት ባለፈም የጨዋታውን የማሳረጊያ ጎል በስሙ አስመዝግቧል፡፡
\"\"
አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ሲዳማ ቡና

ከአስከፊ የውድድር ዘመን በኋላ ለቡድናቸው ሦስተኛ ተከታታይ ድልን ያሳኩት አሰልጣኝ ሥዩም የሳምንቱ ምርጣችን ሆነዋል። ቀደም ባሉት ሁለት ድሎች በተሻለ ነፃነት ወደ ሜዳ የገባው ቡድናቸው ከውጤት ባሻገር ከተገጣሚው የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግም ጭምር ነበር ከወራጅ ቀጠናው በእርምጃዎች ከፍ ያደረገውን ውጤት ማሳካት የቻለው።

ተጠባባቂዎች

ፋሲል ገብረሚካኤል – ባህር ዳር ከተማ
ጊት ጋትኩት – ሲዳማ ቡና
ሐቢብ መሐመድ – ኢትዮጵያ መድን
አብዱልከሪም መሐመድ ኢትዮጵያ ማድን
አቤል እንዳለ – ሲዳማ ቡና
አበባየሁ ዮሐንስ – ሲዳማ ቡና
አደም አባስ – ባህር ዳር ከታማ
ፊሊፕ አጃህ – ሲዳማ ቡና