መረጃዎች | 92ኛ የጨዋታ ቀን

የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን የማያገኙት የ25ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን የሊጉን ጨዋታዎች በተመለከተ ተከታዮቹ መረጃዎች ተሰባስበዋል።

አዳማ ከተማ ከአርባምንጭ ከተማ

በደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ እንዲሁም በወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ ተምጠው ነገ የሚገናኙት አዳማ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ከድል ጋር ዳግም ለመገናኘት የሚያደርጉት የነገ ፍልሚያ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት ይታመናል፡፡

ምንም እንኳን ወደ አስተማማኝ ደረጃ ተጠግቶ ቢቀመጥም ያለፉትን ሶስት ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለው አዳማ ከተማ በቀጣይ ያሉበት ሦስት ጨዋታዎች የመውረድ ስጋት ካለባቸው ክለቦች ጋር ስለሆኑ ከነገ ጀምሮ ፍልሚያዎቹን በተሻለ የትኩረት ደረጃ መቅረብ ይገባዋል። በተለይ የነገ ተጋጣሚው አርባምንጭ ከተማ ደግሞ ያለፉትን ስድስት ጨዋታዎች ስላላሸነፈ ድል ተጠምቶ ስለሚመጣ ቀላል የሚባል ፈተና ላይገጥመው ይችላል። የሆነው ሆኖ ወጣቶችን እና አንጋፎችን አጣምሮ የተገነባው ቡድኑ በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ቢሆንም እንቅስቃሴውን በውጤት የማሳጀብ ብቃቱ ላይ በደንብ መስራት ይገባዋል።
\"\"
ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ስምንት ነጥቦች አስራ አምስቱን የጣለው አርባምንጭ ከተማ ያለበት ቦታ እጅግ አስጊ ነው። እርግጥ ከበላዩ ካለው ክለብ (ወልቂጤ ከተማ) በአራት ነጥብ ብቻ ርቆ ቢቀመጥም አሁን ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ አስጊ ስለሆነ በቶሎ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ይገባዋል። በተለይ ደግሞ ለወትሮ የሚታወቅበትን ጠንካራ የመከላከል አጨዋወት በማጣቱ እየተቸገረ የሚገኝ ሲሆን ይህንን የኋላ ሽንቁር በቶሎ ማስተካከል ይጠበቅበታል። በእንቅስቃሴ ደረጃ የነገ ተጋጣሚው ከኳስ ጋር ማሰለፍ የሚመርጥ ስለሆነ በጋራ በመከላከል በመልሶ ማጥቃት አደጋን ይፈጥራል ተብሎም ይጠበቃል።

አዳማ ከተማ ዳዋ ሆቴሳ ወደ ልምምድ ቢመለስለትም ለጨዋታ አይደርስም ፤ አብዲሳ ጀማል እና ዊሊያም ሰለሞን ደግሞ አሁን ከክለቡ ጋር እንደማይገኙ ተገልጿል።

በሊጉ በ16 ጨዋታዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች አምስት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ 12 ግቦች ያስቆጠሩት አርባምንጮች ስድስት ጊዜ 10 ግብ ያስቆጠሩት አዳማዎች ደግሞ አራት ጊዜ ድል አድርገዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከለገጣፎ ለገዳዲ

በተለያየ መንገድ የሚገኙትና በ23 ነጥቦች ተራርቀው የተቀመጡት ኢትዮጵያ ቡና እና ለገጣፎ ለገዳዲ በመካከላቸው እጅግ የሰፋ ልዩነት ቢኖርም እንደ መጀመሪያው ዙር ጨዋታቸው ጥሩ ፉክክር ሊያደርጉ ይችላሉ።

ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ በ24ኛ የጨዋታ ሳምንት በወራጅ ቀጠናው የሚገኘውን ኢትዮ ኤለክትሪክ የረቱት ኢትዮጵያ ቡናዎች ነገ ደግሞ ሌላኛውን የወራጅ ቀጠና ክለብ ለገጣፎ ለገዳዲን ይፋለማሉ። በኤልፓው ጨዋታ ቡድኑ መጠነኛ የአደራደር እና የሚና ለውጥ አድርጎ ወደ ሜዳ ቢገባም በሚያስበው መልኩ መንቀሳቀስ ያልቻለ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ግን ወደ ቀደመ አሰላለፉ ተመልሶ የተሻለ ለመሆን ሞክሯል። በዚህ ሂደት አሁንም የማጥቃት አጨዋወቱ ላይ ክፍተቶች ያሉበት ቢሆንም የነገ ተጋጣሚው ለገጣፎ በሊጉ በርካታ ግቦችን ያስተናገደ በርቀት ቀዳሚው ክለብ ስለሆነ እምብዛም ላይቸገር ይችላል።
\"\"
በሊጉ በርካታ ሽንፈት (17) እና በርካታ ግብ ያስተናገደ (56) እንዲሁም ያነሰ ግብ ያስቆጠረ (16) ክለብ የሆነው ለገጣፎ ለገዳዲ በሁለተኛው ዙር ውድድር የተነቃቃ ቢመስልም ተጨባጭ የውጤት መሻሻል ሳያሳይ በወራጅ ቀጠናው ቅርቃር እየዳከረ ይገኛል። በብዙ መስፈርቶች እንከኖች ያሉበት ቡድኑ ለከርሞ በሊጉ ለመወዳደር ያለው ዕድል ከሳምንት ሳምንት እየተመናመነ የመጣ ይመስላል። እርግጥ በእንቅስቃሴ ረገድ መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ያለው ጥንካሬ የወረደ በመሆኑ እንቅስቃሴውን በውጤት ማሳጀብ አልቻለም። የጨዋታ ቁጥሮች እያነሱ ስለመጡ ግን ፈተናውን እጅግ ከባድ ያደርግበታል።

ኢትዮጵያ ቡና ገዛኸኝ ደሳለኝ እና አማኑኤል አድማሱን በጉዳት ምክንያት ያጣል። በለገጣፎ ለገዳዲ በኩል በረከት ተሰማ ከጉዳት ሱራፌል አወል ደግሞ ከቅጣት መመለሳቸው ጥሩ ዜና ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖ በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት የመጀመሪያው ዙር ጨዋታ መሸናነፍ አልቻሉም ፤ በውጤቱም ሁለት አቻ ተለያይተዋል።