በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ወሳኝ የሆኑትን የነገ ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።
ባህር ዳር ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
በእስካሁኑ ግንኙነታቸው የአቻ ውጤት የማያውቃቸው ባህር ዳር ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ዘንድሮ በርካታ ግቦችን የሚያስቆጥር እና ጥቂት ግቦች የሚያስተናግድ ቡድን ባህሪን ተላበሰው ነገ 09:00 ሲል ለሁለተኛ ዙር ጨዋታ ይገናኛሉ።
ባሳለፍናቸው ሁለት የጨዋታ ሳምንታት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ከሰባት ወደ ሁለት መቀነስ የቻሉት ባህር ዳር ከተማዎች ነገ ደግሞ ለሰዓታትም ቢሆን በሰንጠረዡ አናት መቀመጥ የሚያስችል ጨዋታ ይጠብቃቸዋል። ከኢትዮጵያ መድን እና ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋሩ በፉክክሩ የመዝለቃቸው ነገር ጥያቄ ውስጥ ገብቶ የነበሩት የጣና ሞገዶቹ በኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማ ላይ ባሳኳቸው ድሎች ኮስታራነታቸውን አሳይተዋል። በተለይም በአዳማ ከተማው ጨዋታ ቡድኑ ከወትሮው አንፃር የማጥቃት ሂደቱ ተዳክሞ ቢታይም በ1-0 ውጤቱን አስጠብቆ የወጣበት መንገድ በበጎ ጎኑ የሚወሰድ ነው። ሆኖም ነጥብ በጣለባቸው ጨዋታዎቹ ላይም በጉልህ ይታይ የነበረው ይህ ድክመት ነገ በጨዋታ በአማካይ 0.65 ብቻ ጎል በሚያስተናግዱት በነብሮቹ ፊት መደገም የማይኖርበት ነው።
የሀዲያ ሆሳዕና የግብ የማስቆጠር ችግር እንደቀጠለ ነው። በሊጉ 19 ግቦች ብቻ ያሏቸው ሀዲያዎች በዚህ ቁጥር የተሻሉ የሆኑት በግርጌ ካለው ለገጣፎ ለገዳዲ ብቻ ነው። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ብቻ ኳስ እና መረብን ማገናኘቱንም እዚህ ጋር ማንሳት ተገቢ ይሆናል። ለነብሮቹ ነገም ይህ ድክመታቸው ሊፈትናቸው እንደሚችል መገማት ቀላል ነው። በሌላ ፅንፍ ደግሞ በሊጉ ጥቂት ግቦች (15) ብቻ በማስተናገድ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የመስተካከላቸው ነገር ትልቁ ጠንካራ ጎናቸው ነው። አሁን ለሚገኙበት 6ኛ ደረጃ ዋስትና የሰጣቸው እንደቡድን የመከላከል ጠጣርነታቸው ግን 43 ግቦችን ካስቆጠረው የጣና ሞገዶቹ የማጥቃት ኃይል ጋር ሲገናኝ ትልቅ ስጋት የሚሆንበት ጉዳይ በቅጣት እና በጉዳት የሚያጣቸው የኋላ ደጀኖቹ ቁጥር መበራከት ነው።
ባህር ዳር ከተማ ጨዋታውን ያለምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና ይከውናል። በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝነት ሹመት የተሰጣቸው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛውም የክለብ ኃላፊነታቸውን ደርበው የሚወጡ በመሆኑ ቡድናቸውን የሚመሩ ይሆናል። በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ግን ፍሬዘር ካሳ ፣ ሔኖክ አርፊጮ ፣ ብርሀኑ በቀለ እና ባዬ ገዛኸኝ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ከመሆናቸው ባሻገር ቃልአብ ውብሸት እና ቤዛ መድህን ጉዳት ላይ ሲገኙ ስቴፈን ኒያርኮ እና ራምኬል ሎክም መመለሳቸው አጠራጣሪ ሆኗል። ለቡድኑ መልካም የሆነው ዜናም የብሩክ ማርቆስ መመለስ ብቻ ሆኗል።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን አምስት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ባህር ዳር ከተማ ሦስት እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና ሁለት ድሎችን አሳክተዋል። በጨዋታቸው ከተቆጠሩ ስድስት ግቦች ውስጥ አራቱ የጣና ሞገዶቹ ሁለቱ ደግሞ የነብሮቹ ነበሩ።
ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ምሽት 12:00 ላይ የሚከናወነው የጦና ንቦቹ እና የፈረሰኞቹ ጨዋታ ወላይታ ድቻን ወደ ሰንጠረዡ ወገብ ከፍ የማድረግ ቅዱስ ጊዮርጊስን ደግሞ መሪነቱን የማስቀጠል ዕድልን ይዞ ይከናወናል።
32 ነጥቦች ላይ የሚገኘው ወላይታ ድቻ የከፋ የመውረድ ስጋት ውስጥ ይገኛል ለማለት ባይቻልም የነጥብ ስብስቡን ከፍ አድርጎ ሙሉ ለሙሉ ራሱን ነፃ ማድረግ እንደሚኖርበት አይካድም። ከለገጣፎ እና መቻል ድሎች በኋላ ሁለት ተከታታይ ነጥቦችን የጣሉት የጦና ንቦቹ አሁንም ወጥ ግብ አስቆጣሪ ያለማግኘታቸው ጉዳይ እንደፈተናቸው ማንሳት ይቻላል። ቡድኑ በሦስቱ የፊት አጥቂዎቹ ቃሊኪዳን ፣ ስንታየሁ እና ዘላለም ያስቆጠራቸው ጎሎች ድምር ከኢስማኤል ኦሮ አጎሮ የጎሎች ብዛት በሰባት የሚያንስ መሆኑ ለዚህ በቂ ማሳያ ይመስላል። በሌላ በኩል እስካሁን 20 ግቦችን ብቻ ያስተናገድው የመከላከል ብርታታቸው ለእንደነገ ዓይነት ከባድ ጨዋታዎች ዋነኛ መተማመኛቸው መሆኑ አይካድም። በመሆኑም በጨዋታው ጥንቃቄን መርጦ በቀጥተኛ ጥቃት ወደ ፊት ለመሄድ የሚሞክር ቡድን ከወላይታ ድቻ የሚጠበቅ ይሆናል።
ፈረሰኞቹ ከአራት ተከታታይ ድሎች በኋላ ባሳለፍናቸው ሁለት የጨዋታ ሳምንታት አምስት ነጥቦችን ጥለው የቻምፒዮንነት ግስጋሴያቸውን ቀዝቅዝ ያደረጉ ይመስላሉ። እየተከተላቸው የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ ቀድሞ በሚጫወትበት የነገው የጨዋታ ዕለት ወደ ድል መመለስ የማያሻማ ግዴታቸው ይሆናል። በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከፍ ባለ ግለት ጨዋታዎችን ጀምረው ግቦችን በማስቆጠር ተጋጣሚ ማንሰራራት እንዳይችል ያረጉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሰሞኑን በማጥቃቱ ረገድ ድክመት እየታየባቸው ይገኛል። የሊጉን ከፍተኛ የግብ መጠን ከማስመዝገባቸው ባለፈ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነ አጥቂ ከመያዛቸው አንፃር በመጨረሻዎቹ ሁለት ግጥሚያዎች አንድ ጎል ብቻ ማስመዝገባቸው እንደ ድክመት የሚነሳ ነው። በተለይም ሰሞኑን ተጋጣሚ ቡድኖች እስማኤል ኦሮ አጎሮን ያነጣጠረ የመከላከል ውቅር ይዘው በመቅረብ ያገኙትን ስኬት ወላይታ ድቻም መከተሉ የሚቀር ካለመሆኑ አንፃር በነገው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት ዕቅድ የተለየ መንገድን ይዞ እንዲቀርብ መነሻ የሚሆን ይመስላል።
ወላይታ ድቻ በነገው ጨዋታ የረጅም ጊዜ ጉዳት ካለበት አንተነህ ጉግሳ በቀር የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማኑኤል ገብረሚካኤልም እንዲሁ ከጉዳቱ ባለመመለሱ ከጨዋታው ውጪ ነው። በሌላ በኩል ከአማኑኤል በተጨማሪ ጉዳት ላይ የሰነበቱት ጋቶች ፓኖም ፣ ሱለይማን ሀሚድ እና ምኞት ደበበ ያገገሙ ሲሆን ለነገው ጨዋታ የመድረሳቸው ጉዳይ ግን እርግጥ አልሆነም።
ከዚህ ቀደም 17 ጊዜ የተገናኙት ሁለቱ ተጋጣሚዎች አራት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ 8 ወላይታ ድቻ ደግሞ 5 ድሎችን አሳክተዋል። በጨዋታዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስ 23 ወላይታ ድቻ ደግሞ 13 ጎሎች አሏቸው።