ሪፖርት | ለገጣፎ ለገዳዲ ባደገበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊጉ የሚያወርደውን ውጤት አስመዝግቧል

ኢትዮጵያ ቡናን ከለገጣፎ ለገዳዲን ያገናኘው የምሽቱ መርሐግብር 1-1 ተጠናቋል። ውጤቱም ለኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ 11ኛ የአቻ ውጤቱ ሆኖ ሲመዘገብ ለገጣፎ ለገዳዲን ደግሞ ወደ ከፍተኛ ሊጉ አውርዷል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ የኢትዮጵያ ቡና እና የለገጣፎ ለገዳዲ ጨዋታ ሲደረግ ቡናዎች በ 24ኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1-0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ አብዱልከሪም ወርቁን አስወጥተው ብሩክ በየነን በማስገባት ሲጀምሩ ለገጣፎዎች በበኩላቸው በተመሳሳይ ሳምንት በፋሲል ከነማ 2-0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ተስፋዬ ነጋሽ እና ጋብሬል አህመድ በ አስናቀ ተስፋዬ እና ካርሎስ ዳምጠው ቦታ ተተክተው ጀምረዋል።

\"\"

ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ መኃል ሜዳው ላይ ከተደረገው ፉክክር ውጪ በሁለቱም በኩል በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። ሆኖም ለገጣፎ ለገዳዲዎች 3ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ሲያደርጉ አማኑኤል አረቦ ከረጅም ርቀት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ይዞበታል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች በመስመር የተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተደራጅተው ለመግባት ሲቸገሩ ለገጣፎ ለገዳዲዎች 23ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት በጋብሬል አህመድ አማካኝነት ግሩም ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው በረከት አማረ መክኖባቸዋል። በሁለቱም በኩል ደካማ እንቅስቃሴ የታየበት የመጀመሪያ አጋማሽም የተለየ ነገር ሳያስመለክተን ተገባዷል።


ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል 55ኛው ደቂቃ ላይ ለገጣፎዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። መሐመድ አበራ ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው አማኑኤል አረቦ ከግራው የሜዳ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ኢትዮጵያ ቡናዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተሻለ የጨዋታ ስሜት ሲቀጥሉ ኢብሳ በፍቃዱ በግራ መስመር ካደረገባቸው ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ በቀር በጨዋታው ብልጫ መውሰድ ሲችሉ 79ኛው ደቂቃ ላይም የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ኃይለሚካኤል አደፍርስ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ያገኘው መሐመድኑር ናስር በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።


የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በጨዋታው ሙሉ ነጥብ ለማሳካት ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ቡናዎች ጨዋታውን መምራት ሊጀምሩ ተቃርበውም መስፍን ታፈሰ በግራ መስመር ያገኘውን ያለቀለት አጋጣሚ ግብ ጠባቂው ኮፊ ሜንሳህ አምክኖበታል።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ያሳለፉት ለገዳዲዎች 92ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የወሰዱትን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው መሐመድ አበራ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሆኖም በአንድ ደቂቃ ልዩነት ኢትዮጵያ ቡናዎች ከቅጣት ምት በኃይለሚካኤል አደፍርስ አማካኝነት ሙከራ አድርገውም ግብ ጠባቂው ኮፊ ሜንሳህ መልሶታል። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ለገጣፎ ለገዳዲ አምስት የጨዋታ ሳምንታት  እየቀሩት በመጣበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊጉ መውረዱን አረጋግጧል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የለገጣፎ ለገዳዲው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ በጨዋታው ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት እና የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሞከሩ ሲናገሩ ካለፉት ሳምንታት ተሻሽለው እንደቀረቡ በመግለጽ ማሸነፍ እንደነበረባቸው እና ይህንን ውጤትም እንደሚቀበሉ ገልፀዋል። አሰልጣኙ አክለውም በሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ የተጫዋቾቹ ልምድ ማነስ ተጨምሮበት የተሳካ እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን ድል ላለመቀዳጀታቸው እንደምክንያት ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በበኩላቸው ተጋጣሚያቸውን እንደጠበቁት ማግኘታቸውን በመጠቆም ከዕረፍት በፊት የተከፈቱ ቦታዎችን ለማግኘት ቢጥሩም እንዳላገኙ ይህንንም በሁለተኛው አጋማሽ አሻሽለው እንደቀረቡ ሲናገሩ ቡድናቸው ደካማ የሚባል አቀራረብ ባይኖረውም የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ክፍት  የመጫወቻ ቦታ አለመስጠታቸው እነርሱን ደካማ እንዳስመሰላቸው በመግለጽ በዚህም የተጋጣሚ ቡድን እንቅስቃሴ ጠንካራ እንደነበርም ጠቁመዋል።