የአሰልጣኞች አስተያየት| ባህርዳር ከተማ 1-2 ሀድያ ሆሳዕና

\”ተጫዋቾቼ ውጤቱን ለመቀየር የተጫወቱበት መንገድ ሳላደንቅ አላልፍም\” ደግአረግ ይግዛው

\”በዚህ ስብስብ ይሄን ውጤት ማስመዝገባችን ጥሩ ነው\” ያሬድ ገመቹ

ባህር ዳር ከተማ ከአስራ ሁለት ጨዋታዎች በኋላ ሽንፈት ባስተናገደበት ጨዋታ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡትን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ግን በዝናብ ምክንያት ሜዳው መበላሸቱ ባሰብነው መንገድ እንዳንጫወት ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። ተጫዋቾቻችን ዘጠና ደቂቃ ሙሉ የሚችሉትን አድርገዋል። ዛሬ ነጥብ ብንጥልም ቀጣይ ግን ክፍተታችን አስተካክለን እንመለሳለን።

\"\"

ስለ ቡድኑ በፊት መስመር የነበረው ስልነት መቀነስ…

የሚያጋጥም ነገር ነው ፤ ዛሬም ጥሩ እንቅስቃሴ ነው ያደረጉት። ግን ጎሎች ያስተናገድንበት መንገድ ጥሩ ሆነን ጫና በፈጠርንበት ሰዓት ነው። አንዳንዴ ትኩረት ማጣት አለ። የመጀመርያው ጎል ስናስተናግድ መቆጣጠር የምንችልበት ዕድል ነበር ግን አልሆነም በአጠቃላይ ግን ተጫዋቾቼ ውጤቱን ለመቀየር የተጫወቱበት መንገድ ሳላደንቅ አላልፍም። ጥረት አድርገዋል ፤ ያሸነፈው ሀድያም እንኳን ደስ አላቹ ማለት እፈልጋለሁ።

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ

ስለ ጨዋታው…

እጅግ ፈታኝ ጨዋታ ነበር። ሊጉን በመምራት ላይ ካሉት ቡድኖች አንዱ ነው ፤ የስብስቡ ጥራትም ከፍተኛ ነው። ከዛ በተጨማሪ ስድስት እና ከዛ በላይ ተጫዋቾች በጉዳት እና በቅጣት አላሰለፍንም። በዚህ ስብስብ ይሄን ውጤት ማስመዝገባችን ጥሩ ነው።

ከዕረፍት መልስ ስለተወሰደባቸው ብልጫ…

ጉጉት ነበር ፤ ተጫዋቾቹም ልምድ የላቸውም። ውጤቱን ለማስጠበቅ ማፈግፈጋቸው ጫና ውስጥ ከተተን። ማፈግፈጋችን ተከትሎ የመጣ ጫና ነው።

\"\"