ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

ፈረሰኞቹ የጦና ንቦቹን 2ለ1 በመርታት መሪነታቸውን በአምስት ነጥቦች አስፍተዋል።

\"\"

ሁለቱ ቡድኖች በ24ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታቸው ከተጋጣሚያቸው ጋር ነጥብ በተጋሩባቸው ወቅት ከተጠቀሙት አሰላለፍ በተመሳሳይ የአንድ ተጫዋች ለውጥን አድርገዋል። ወላይታ ድቻ አናጋው ባደግን በደጉ ደበበ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩላቸው ዳዊት ተፈራን በአቤል ያለው ለውጠዋል።

ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ካልሆነ በስተቀር ከሙከራዎች አኳያ አይን አፋር የነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ ፈረሰኞቹ መነሻቸውን ከመሐል ክፍሉ አድርገው ወደ ሁለቱ መስመሮች በመለጠጥ ጥቃትን ለመሰንዘር ሲጥሩ ስንመለከት በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች የኋላ በራቸው ሸፍነው ነገር ግን ኳስን በሚያገኙበት ወቅት በፈጣን መልሶ ማጥቃት ዘላለም አባተ እና ቢኒያም ፍቅሬን ለመጠቀም ጥረቶችን ሲያደርጉ ተመልክተናል። በአጋማሹ በርካታ ተመልካቾች ሜዳ ላይ ክለቦቻቸው ሲደግፉ ከሚታየው ግሩም የሆነ ድባብ ውጪ የጠሩ አጋጣሚዎችን ጨዋታው ሊያሳየን አልቻለም።

\"\"

ጨዋታው 36ኛው ደቂቃ ላይ እንደደረሰ ወላይታ ድቻዎች የቀኝ መስመር ተከላካያቸው ያሬድ ዳዊት በሁለት ቢጫ በቀይ አጥተዋል። ተጫዋቹ አቤል ያለው ላይ የሰራው ጥፋት በቀይ ከሜዳ ለመሰናበቱ ምክንያት ነበር። የወላይታ ድቻን መጉደል ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከመስመር እና ከቆሙ ኳሶች እስማኤል ኦሮ አጎሮን ትኩረት ያደረጉ ኳሶች በድግግሞሽ በመጣል ጎል እና መረብን ለማገናኘት ቢታትሩም ጨዋታው የጠራ የግብ ዕድልን ማሳየት ተስኖት ወደ መልበሻ ክፍሎ ጨዋታው ያለ ጎል አምርቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ተከላካያቸውን በቀዳሚው አጋማሽ በቀይ ያጡት ድቻዎች አጥቂው ቃልኪዳንን ዘላለምን በአናጋው ባደግ በመቀየር ነበር ወደ ሜዳ የተመለሱት።

\"\"

ጠንከር ባለ ስሜት የቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ፈረሰኞቹ አመዛኙን የጨዋታ መንገድ በሔኖክ አዱኛ የቀኝ የሜዳው ክፍል በማጋደል ወደ ሳጥን ውስጥ በሚላኩ ኳሶች የጎል ቀዳዳ ፍለጋን ቶሎ ቶሎ በወጥነት ተግባራዊ ሲያደርጉ ድቻዎች በአንፃሩ አሁንም በሽግግር የመልሶ ማጥቃት አጨዋወታቸው ጥቂትም ቢሆንም የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን ፈትነዋል። በወላይታ ድቻ በኩል ዘላለም አባተ ከረጅም ርቀት እየገፋ ገብቶ ከሳጥኑ ጠርዝ ወደ ጎል ሲመታ ለጥቂት የወጣችበትን እና ፍሪምፓንግ ለግብ ጠባቂው ባህሩ አቀብላለው ብሎ የተሳሳተውን ዘላለም አግኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረችዋ ሌላኛዋ የቡድኑ ሙከራ ነበረች።

የጨዋታው ደቂቃ በገፋ ቁጥር ጨዋታውን ወደ ቁጥጥራቸው ስር የከተቱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሔኖክ አዱኛ ሁለት ጊዜ ወደ ጎል በቀጥታ ሲመታ ቢኒያም ገነቱ አከታትሎ ከመለሳቸው በኋላ ሦስተኛው ኳሱ ወደ ጎልነት ተለውጣለች።

\"\"

62ኛው ደቂቃ ሔኖክ በረጅሙ ወደ ጎል ሲያሻማ ቸርነት ጉግሳ የልጅነት ክለቡ ላይ በግንባር ከመረብ ደባልቋታል። ተጫዋቹም በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ወላይታ ድቻ ጎል አስቆጥሯል። በቀሩት የጨዋታ ደቂቃ ወላይታ ድቻ በዮናታን ኤልያስ አማካኝነት የሚያስቆጭ ዕድል ካመለጣቸው በኋላ በተቃራኒው ሁለተኛ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። 78ኛው ደቂቃ በረጅሙ ወደ ጎል ሲሻማ አዲስ ግደይ በግንባር ገጭቶ ብረት ሲመልሳት የድቻ ተከላካዮች ለማውጣት ሲጥሩ እስማኤል ኦሮ አጎሮ ኳሷ ነክቷት ጎል ሆናለች።

\"\"

ጎል ካስተናገዱ በኋላ የመጨረሻውን አስር ደቂቃ ተጭነው የተጫወቱት ድቻዎች 82ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ዮናታን ኤልያስ ሲያሻማ በረከት ወልደዮሐንስ በግንባር ገጭቶ አስቆጥሯታል። አቻ ለመሆን ድቻዎች በዘላለም ጊዮርጊሶች ተጨማሪ ጎል ለማስቆጠር በበረከት አማካኝነት ሙከራ ቢያደርጉም ጨዋታው በፈረሰኞቹ 2ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።