መረጃዎች | 94ኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ፋሲል ከነማ ከ ሲዳማ ቡና

9 ሰዓት ላይ የሚጀመረው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር 37 ነጥቦችን በመያዝ 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ፋሲል ከነማዎች በ 30 ነጥቦች 12ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ጋር ሲያገናኝ ሁለቱም ቡድኖች ያሉበትን ወቅታዊ የአሸናፊነት መንፈስ ለማስቀጠል ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከተከታታይ ሁለት ድሎች በኋላ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ዐፄዎቹ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ግን በሱራፌል ዳኛቸው ሁለት ግሩም ግቦች ለገጣፎ ላይ ሙሉ ነጥብ መውሰድ ሲችሉ በነገው ዕለትም ከተከታታይ ሦስት ወሳኝ ድሎች ከሚመለሱት ሲዳማዎች ላይም ድል ለመቀዳጀት ጠንካራ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል። ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አራቱን መርታት የቻሉት ፋሲሎች ከነበሩበት የደረጃ ሠንጠረዡ ወገብ ከፍ በማለት ከኢትዮጵያ መድን ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሰባት በማጥበብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ የነገውን ጨዋታ ካሸነፉ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ባህርዳር ከተማ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ 10 በማጥበብ የኮንፌዴሬሽን እና የሜዳሊያ ደረጃውን በማለም ወደ አሸናፊነት ይመለሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው አማካዩ ሱራፌል ዳኛቸው በነገው ጨዋታም ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"

በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ታጅበው መጫወት በጀመሩበት ቅፅበት ከድል ጋር በመታረቅ ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስተኛ ተከታታይ ድላቸውን የተቀዳጁት ሲዳማዎች ከወራጅ ቀጠናው በመሸሽ መጠነኛ እፎይታን ሲያገኙ የነገውን ጨዋታ መርታትም ከወራጅ ቀጠናው በሰባት ነጥቦች በመራቅ የተደላደለ ደረጃ ላይ  እንዲቀመጡ ያደርጋቸዋል። ረፍት የለሽ በሆነ እንቅስቃሴ ከፍተኛ የማሸነፍ ፍላጎት የሚታይበት ቡድኑ በሁለተኛው ዙር ባስፈረሙት ፊሊፕ አጃህ ብቸኛ ግቦች ማሸነፉ ግን ተጋጣሚዎች ለእርሱ ቦታ ላለመስጠት አስበው በሚገቡት ጊዜ ግብ አስቆጣሪ የሚሆን አማራጭ ምንጭ ያስፈልጋቸዋል። በውድድር ዓመቱ ተጠባቂ የነበረው አጥቂያቸው ይገዙ ቦጋለም ከ 7 ግቦች እና 2 ለግብ አመቻትቶ ካቀበላቸው ኳሶች የበለጠ በግቦች ላይ ተሳታፊ አለመሆኑ ለቡድኑ የግብ ዕጥረት እንደ ምክንያት ይጠቀሳል።

በሲዳማ ቡና በኩል ሙሉቀን አዲሱ ከቅጣት ሲመለስ ቴዎድሮስ ታፈሰ ፣ ሙሉዓለም መስፍን እና ሳላሀዲን ሰይድ ወደ ልምምድ ቢመለሱም መሰለፋቸው አጠራጥሯል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አሥራ አንድ (11) ጨዋታዎች አንድም በአቻ የተጠናቀቀ ጨዋታ የሌለ ሲሆን አሥራ ዘጠኝ(19) ግቦች ያሉት ፋሲል ከነማ ለሰባት(7) አሥራ ሦስት(13) ግቦች ያሉት ሲዳማ ቡና ደግሞ ለአራት(4) ጊዜያት አሸንፈዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ምሽት 12 ሰዓት ላይ ወልቂጤ ከተማን ከድሬዳዋ ከተማ የሚያገናኘው መርሐግብር ሁለቱም ቡድኖች ካንዣበባቸው የመውረድ አደጋ ለመሸሽ በሚያደርጉት ብርቱ ፉክክር ይጠበቃል።

ካለፉት አሥር ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ በመርታት በአጠቃላይ ዘጠኝ ነጥቦችን ብቻ ያሳኩት ወልቂጤዎች ሜዳ ላይ የሚያሳዩትን ጠንካራ እንቅስቃሴ ቁጥሮች አይደግፉላቸውም። ለገጣፎ ለገዳዲን ከ 2-0 መመራት ተነስተው 3-2 ማሸነፋቸው ትልቅ መነቃቃት ፈጥሮላቸው ወደ ድል ይመለሳሉ ተብሎ ቢታሰብም ባለፈው ሳምንት ግን ከ 75 ደቂቃዎች በላይ የተጫዋች ቁጥር ብልጫ በወሰዱበት የሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ የግብ ዕድሎችን ባለመጠቀማቸው ድል ሳያሳኩ ቀርተዋል። ከወራጅ ቀጠናው ሦስት ነጥቦችን ብቻ ርቀት የተቀመጡት ሠራተኞቹ ካሉበት ደረጃ ለመሸሽም የነገው ጨዋታ ውጤት ያስፈልጋቸዋል። ሆኖም ተጋጣሚያቸው ድሬዳዋ ከተማ ከነርሱ በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ መቀመጡም በያዝው ተመሳሳይ ዓላማ ፈታኝ ሆኖ ሊቀርብባቸው ይችላል።

\"\"

እንደ ተጋጣሚያቸው ወልቂጤ ከተማ ሁሉ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ የገቡት ብርቱካናማዎቹ ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ መርታት ሲችሉ አራቱን ተሸንፈዋል። ይህ ውጤትም ከወራጅ ቀጠናው በአራት ነጥቦች ብቻ ከፍ ብለው እንዲቀመጡ አድርጓል። በሊጉ ከለገጣፎ ለገዳዲ (57) በመቀጠል ሁለተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (39) ያስተናገዱት ድሬዎች ተገማች በሆነ አቀራረባቸው ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን የ 3-0 ሽንፈት እንዲያስተናግዱ ምክንያት ሆኗል። ሆኖም በነገው ዕለትም የሊጉን ሁለተኛ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የሆነውን ጌታነህ ከበደ ከያዙት ወልቂጤዎች ሙሉ ነጥብ ለማሳካት የኋላ መስመራቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በወልቂጤ ከተማ በኩል ተመስገን በጅሮንድ፣ አፈወርቅ ኃይሉ፣ ፍፁም ግርማ፣ አዳነ በላይነህ እና አቡበከር ሳኒ በጉዳት ዋሃቡ አዳምስ ደግሞ በቅጣት ጨዋታው የሚያልፋቸው ሲሆን አኑዋር ዱላ ተመልሷል። ያሲን ጀማል፣ ብሩክ ቃልቦሬ፣ ያሬድ ታደሰ እና ከድር አዩ ደግሞ በጨዋታው የማይገኙ የድሬዳዋ ተጫዋቾች ናቸው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ አምስት ጊዜያት(5) ተገናኝተው ሁለቱ ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሁለት ጨዋታዎች በአቻ አንዱ ጨዋታ ደግሞ በድሬዳዋ አሸናፊነት ተጠናቋል። ወልቂጤ ስምንት (8) ድሬዳዋ ደግሞ ስድስት (6) ግቦችንም ማስቆጠር ችለዋል።