የአሰልጣኞች አስተያየት | ፋሲል ከነማ 0-1 ሲዳማ ቡና

\”የዛሬው ድል ትልቅ ነው ፤ ከመውረድ ስጋት ተላቀን ወደፊት እየተጠጋን ነው።\” አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ

\”መጀመሪያ ምልመላ ላይ ነው ሥራዎች የተበላሹት ስለዚህ ባለን ነገር ለማስተካከል እንሄዳለን።\” አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ

ሲዳማ ቡና አራተኛ ተከታታይ ድሉን ፋሲል ከነማን 1ለ0 በማሸነፍ ካስመዘገበበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የሁለቱም ክለብ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ ሀሳባቸው አጋርተዋል።

አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ

ስለ ጨዋታው…

\”ጨዋታው ጥሩ ነው። በተለይ ፋሲል ጠንካራ ቡድን ነው ፤ ዛሬ ይሄን ነጥብ ብናገኘው ከሌሎች ቡድኖች የበለጠ ከፍ ስለምንል አሁንም የበለጠ ከፍታችን እየሄደ ነው ያለው ፤ ይሄ ለቡድኑ ትልቅ በራስ መተማመን የሚፈጥር ነው። አራት ጨዋታዎችን አድርገን አራቱንም ጨዋታዎች 100% አሳክተናል። የሚቀረን ሁለት ጨዋታ ነው እነሱን በዚህ መነቃቃት ጥሩ ሥራ እንሠራባቸዋለን ብዬ ነው የማስበው።\”

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ስለተወሰደባቸው ብልጫ…

\”እኛ የያዝነውን ውጤት ማስጠበቅ እንፈልጋለን ፤ ተጋጣሚያችን ፋሲል ከነማ ደግሞ ተጭኖ መጫወት አለበት እና ይሄ የሚጠበቅ ነው። እኛ እየተከላከልን በምናገኛቸው ክፍተቶች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እየሄድን ለመጫወት ነው ጥረት ያደረግነው። በአጠቃላይ ያለህን ነገር አስጠብቀህ መውጣት በራሱ ትልቅ ነገር ነው። የዛሬው ድል ትልቅ ነው ከመውረድ ስጋት ተላቀን ወደፊት እየተጠጋን ነው።\”

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ

ስለ ጨዋታው…

\”ገና በአንድ ደቂቃ ነው ግብ የተቆጠረብን ፤ ይህ ደግሞ በተጫዋቾቹ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ አለ። ከዛ ውጪ በጣም ጥሩ ነበር። ያገኘናቸውን የግብ ዕድሎች አልተጠቀምንም እንጂ ጨዋታውን በምንፈልገው መንገድ ነው ያስኬድነው።\”

በሁለተኛው አጋማሽ ስለ ታየባቸው የአጨራረስ ድክመት…

\”እንግዲህ ባሉህ ተጫዋቾች ነው የምትሄደው። ካሉን ልጆች ውጪ ምንም ማድረግ አልችልም። በርካታ ግብ የሚሆኑ ዕድሎችን አግኝተናል ፤ ግን ወሳኝ አጥቂዎች ከሌሉ ምንም ማድረግ አይቻልም። የተቻለኝን ለማስተካከል እሞክራለሁ። መጀመሪያ ምልመላ ላይ ነው ሥራዎች የተበላሹት ስለዚህ ባለን ነገር ለማስተካከል እንሄዳለን።\”

\"\"

በቡድናቸው ላይ ስላላቸው ስሜት…

\”እኛ ቤት የተለመደው ቻምፒዮን መሆን ነው። ደጋፊም የሚፈልገው ያንን ነው። ለውጡን ተመልካቹም ፣ ደጋፊውም ፣ አመራሩም ይረዳዋል ብዬ አስባለሁ። ግን የሚፈለገውን ያህል ባለመሄዱ ከውጤት አንጻር የሚሰማህ ነገር አለ ፤ የቡድኑ ለውጥ ግን ጥሩ ነው ባይ ነኝ።\”