አርባምንጭ ከተማ አሰልጣኙን በማሰናበት ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሾሟል።
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከወረደ በኋላ በድጋሚ 2013 ላይ ወደ ሊጉ የተመለሰው አርባምንጭ ከተማ ከከፍተኛ ሊጉ ካሳደጉት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋር ከአምስት ዓመታት በኋላ ተለያይቷል።
በዘንድሮው የ2015 የሊጉ ጨዋታዎች ደካማ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ክለቡ ካደረጋቸው 25 ጨዋታዎች በደረጃ ሰንጠረዡ በ26 ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ መቀመጡ አሰልጣኙ ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች በደጋፊው መሰማቱን ተከትሎ ነው አሰልጣኙ እና ክለቡ በዛሬው ዕለት መለያየታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ያረጋገጠችው። ከዋና አሰልጣኙ በተጨማሪ ምክትሉ አበው ታምሩ እና ቡድን መሪው ተሾመ ሙሉነህም ሲለያዩ የስፖርት ሳይንስ መምህሩ ፕሮፌሰር አይቸው አባይ ደግሞ ቴክኒክ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።
በቀጣዮቹ አምስት የሊግ ጨዋታዎች ክለቡን በሊጉ ለማቆየት የቀድሞው የክለቡ የአማካይ ተከላካይ እና የክለቡ የወጣት ቡድን አሰልጣኝ በረከት ደሙ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆኖ መሾሙም ታውቋል። በተጨዋችነት ዘሙኑ የቡድኑ አምበል የነበረው የአሁኑ አሰልጣኝ በ2009 የጳውሎስ ፀጋዬን ፣ በ2010 ደግሞ የፀጋዬ ኪዳነማርያምን ስንብት ተከትሎ የክለቡ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆኖ መስራቱ ይታወሳል።