ድሬዳዋ ከተማ በእያሱ ለገሠ እና ሱራፌል ጌታቸው ግቦች ወልቂጤ ከተማን 2-1 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው በይበልጥ ከፍ ብለዋል።
ወልቂጤ ከተማ ከሀድያው የአቻ ውጤቱ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥን አድርጓል። የኋላሸት ሰለሞን ፣ ፍፁም ግርማ እና ብዙአየው ሰይፉን በተመስገን በጅሮንድ ፣ ማቲያስ ወልደአረጋይ እና ተስፋዬ መላኩ ሲተኩ በመድን ሽንፈት ከገጠመው ስብስቡ ድሬዳዋ ከተማ መሳይ ፓውሎስን በአሳንቴ ጎድፍሬድ ፣ ሱራፌል ጌታቸውን በዮሴፍ ዮሐንስ እና ሙኸዲን ሙሳን በሔኖክ ሀሰን ለውጧል።
ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሒደት ግን የተገደቡ እንቅስቃሴዎች የተበራከቱበት ነበር። ጨዋታው እንደተጀመረ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት በቀጥታ የሞከራትን ኳስ ዳንኤል ተሾመ በያዘበት ቅፅበት ወደ ግብ ተጠግተዋል። ወልቂጤ ከተማዎች ኳስን ረጅም ደቂቃ በሚይዙ አማካዮቻቸው ታግዘው የቁጥጥር ድርሻውን በእጃቸው ማስገባት ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ግን ደካሞች ነበሩ። በሽግግር የጨዋታ መንገድ አጥቂው ቢኒያም ጌታቸው ላይ ያነጣጠረ ጨዋታ የተከተሉት ድሬዎች 11ኛው ደቂቃ ላይ በዚሁ የጨዋታ ሒደት ቢኒያም ጥሩ ዕድል አግኝቶ ጀማል ጣሰው ቅልጥፍናውን ተጠቅሞ ኳሷን ከጎልነት አድኗታል።
አቤል ነጋሽ ከጨዋታ ውጪ በሆነ አቋቋም ካስቆጠራት ጎል ውጪ በቀላሉ የድሬዳዋነን የኋላ መስመር መሻገር የከበዳቸው ወልቂጤዎች በተቃራኒው ከቆመ ኳስ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። 38ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሜዳው አቅጣጫ ወደ መስመር ካደላ ቦታ ላይ የተገኘን የቅጣት ምት እንየው ካሳሁን ሲያሻማ እያሱ ለገሠ በግንባር ገጭቶ ጀማል መረብ ላይ መዳረሻዋን አድርጓል። አጋማሹም ከነበረው የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ አንፃር በ1-0 የድሬዳዋ መሪነት ተጋምሷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ወልቂጤ ከተማዎች ወደ ጨዋታው ራሳቸውን በደንብ ለማስገባት የኋላሸት ሰለሞንን በማስገባት የአጥቂ ቁጥራቸውን ከፍ ማድረግ ቢችሉም ሁለተኛ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። 53ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሳሁን በጥሩ የጨዋታ ፍሰት ያገኛትን ኳስ ከተከላካዮች መሐል ለተገኘው ሱራፌል ጌታቸው አቀብሎት አማካዩ ወደ ጎልነት ለውጧታል። ኳሱን በመቆጣጠር በቀላሉ ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ለመግባት ወልቂጤዎች ባይቸገሩም የሚታይባቸው ደካማ አጨራረስ በቀላሉ ጎል እንዳያገኙ የዳረጋቸው ሆኗል።
58ኛው ደቂቃ ከኤፍሬም ዘካሪያስ የደረሰችውን ኳስ አቤል ነጋሽ ወደ ጎል ሞክሮ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ መልሶበታል። ሁለት ጎልን ለማስተናገድ የተገደዱት ወልቂጤ ከተማዎች ተጨማሪ የአጥቂ ክፍል ተጫዋችን በማስገባት በቀሩት ደቂቃዎች በብርቱ መታገል ቢችሉም ከወትሮ የሚታይባቸው አለመረጋጋቶች በቀላሉ ዋጋ ያስከፈላቸው ቢሆንም የኋላ ኋላ ጎል አስቆጥረዋል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዮሐንስ በሳጥን ውስጥ ጌታነህ ከበደ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ጌታነህ በቀላሉ ቡድኑን የምትመልስ ጎል አድርጓታል። በጨዋታው መገባደጃ ላይ ዮሴፍ ዮሐንስ በመልሶ ማጥቃት ካገኛት አጋጣሚ ውጪ ሁለተኛ ጎልን ካስቆጠሩ በኋላ የወልቂጤን ተሻጋሪ ኳሶች መከላከል ላይ ተጠምደው የዋሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ተሳክቶላቸው በመጨረሻም 2ለ1 አሸንፈው ወጥተዋል።