\”ተጫዋቾቼ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ውጤቱን ማግኘት ችለናል\” አሰልጣኝ አስራት አባተ
\”የኔ ሥራ የጎል ዕድሎች እንዲፈጠሩ ማመቻቸት ነው እንጂ ጎል እንዴት እንደሚያገቡ አልነግርም\”
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ
በተቀራራቢ ደረጃ የነበሩትን ሁለት ቡድኖች ያገናኘው እና ተጠባቂ የነበረው ጨዋታ በብርቱካናማዎቹ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ አስራት አባተ – ድሬዳዋ ከተማ
ስለ ጨዋታው…
\”በጣም ጠንካራ ጨዋታ ነበር። ሁለታችንም የነበርንበት ሁኔታ አስጊ ስለ ነበር ፤ ነጥባችንም ተመሳሳይ ነበር። ይሄን ጨዋታ ማሸነፍ ይገባን ነበር ተጫዋቾቼ ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ውጤቱን ማግኘት ችለናል\”።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ስለደረሰባቸው ጫና..
\”ሁለት ለባዶ ከመራን በኋላ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ነው አስበን ነው የገባነው። ተከላካዮቻችን ወደ ኋላ ተስበው እንዲጫወቱ ስላደረግን እና እሱን ተከትሎ በሙሉ አቅም ሊያጠቁ ችለዋል\”።
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – ወልቂጤ ከተማ
ስለ ጨዋታው…
\”ጥሩ ተጫውተናል አልልም ፣ ይሄ ጨዋታ ለሁለታችን ወሳኝ ስለነበር የተሻለ ነገር ለማግኘት ነበር የመጣነው ፤ ሜዳ ላይ መተግበር ግን አልቻልንም። ታክቲካዊ ስህተቶች ሰርተናል ፤ ብዙ ስህተት በፈጠርክ ቁጥር ደግሞ ተጋጣሚህ ያነሰ ስህተት ሰርቶም ያሸንፍሃል\”።
ዘግይተው ጫና ስለፈጠሩበት ምክንያት…?
\”በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ነው ይህ ችግር የታየብን ፣ የኔ ሥራ የጎል ዕድሎች እንዲፈጠሩ ማመቻቸት ነው እንጂ ጎል እንዴት እንደሚያገቡ አልነግርም። ቦታውን አይተው የሚሰሩት ሥራ ነው። ስለዚህ ጉጉትም ተነሳሽነትም አንዳንዴ ይበዛል እሱ ነው ያስተዋልኩት ነገር።\”