መረጃዎች | 95ኛ የጨዋታ ቀን

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሣምንት ማገባደጃ የሆኑትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!

ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን

9 ሰዓት ሲል የሚደረገው የቀኑ የመጀመሪያ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማን ከኢትዮጵያ መድን ሲያገናኝ ኃይቆቹ እጅግ ከናፈቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ መድኖች ደግሞ ከመሪዎቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች መልስ ከሀዲያ እና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ የተጋሩት ሀዋሳዎች ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማቸው ሲያመራ በበርካታ ደጋፊዎቻቸው ታግዘው ድል ያሳካሉ ተብለው ቢጠበቁም ካደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ግን ማግኘት የቻሉት ሁለት ነጥብ ብቻ መሆኑ ቡድኑ ያለበትን የውጤት ማጣት ቀውስ ይጠቁማል። በተለይም እጅግ ደካማ እየሆነ የመጣው የፊት መስመራቸው በአምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስቆጠሩ ወደ ሜዳሊያ ደረጃው ተጠግቶ የነበረውን ቡድን ከወራጅ ቀጠናው በሰባት ነጥቦች ብቻ ርቆ እንዲቀመጥ አስገድዷል። ሆኖም ባለፈው ሳምንት ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲጫወቱ የነበራቸው ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት በነገው ዕለትም ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት አስበው ከሚገቡት እና ፈታኝ ፉክክር እንደሚያደርጉ ከሚጠበቁት ኢትዮጵያ መድኖች ጋርም ይደግሙታል ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"
በሲዳማ ቡና ከገጠማቸው ሽንፈት በማገገም ባለፈው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማ ላይ የ 3-0 ድል የተቀዳጁት መድኖች ምክትል አሰልጣኛቸው ለይኩን ታደሰ ከጨዋታው በኋላ እንደሰጡት አስተያየት የተጋጣሚያቸውን አቀራረብ ቀድመው በመረዳት ሜዳ ውስጥ ያሳዩት እንቅስቃሴ እጅግ የሚደነቅ ነበር። ሁለት ከአሥር ግቦች በላይ ያስቆጠሩ (ብሩክ ሙሉጌታ እና ሐቢብ ከማል) ተጫዋቾችን በብቸኝነት የያዘው ቡድኑ ከተከታታይ ስምንት ጨዋታዎች በኋላ ግቡን ሳያስደፍር መውጣቱም የሚፈልገው ጥንካሬው ነበር። ከነሱ ከፍ ብሎ የተቀመጠው ባህርዳር ከተማ ትናንት በሀዲያ መረታቱን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን ወደ ሦስት ለማጥበብም በነገው ጨዋታ በሜዳቸው እና በደጋፊያቸው ፊት እጅግ ወሳኝ የሆነ ድል ለመቀዳጀት አስበው ከሚገቡት ሀዋሳዎች ጋር ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ብርሀኑ አሻሞ በጉዳት በረከት ሳሙኤል ደግሞ በቅጣት ጨዋታው የሚያልፋቸው ሲሆን ወንድማገኝ ኃይሉ በበኩሉ በውል ምክንያት ከክለቡ ጋር እንደማይገኝ ታውቋል። በኢትዮጵያ መድን በኩል ወገኔ ገዛኸኝ ጉዳት ላይ በመሆኑ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን ኪቲካ ጅማ ከቅጣቱ ይመለሳል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ ሃያ አምስት (25) ጊዜያት ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ ለ አሥራ ሁለት (12) ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ለ አራት (4) ጊዜያት ድል ሲያደርጉ ዘጠኙ ጨዋታዎች በአቻ የተጠናቀቁ ነበሩ። በጨዋታዎቹም ሀዋሳ ሠላሳ ሁለት (32) ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ሃያ ሦስት (23) ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መቻል

የጨዋታ ሳምንቱ የመዝጊያ ፍልሚያ የሆነው የኤሌክትሪክ እና የመቻል ጨዋታ ምናልባት አንዱን የወራጅ ክለብ ሊያሳየን የሚችልበት ዕድል ሲኖር መቻልም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርገው ትግል ይጠበቃል።

እስካሁን በሊጉ ብቸኛ አንድ ጨዋታ ብቻ የረታ ክለብ የሆነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለበርካታ ሳምንታት ከዳከረበት የወራጅ ቀጠና ሳይወጣ የውድድሩ ዓመቱ ሊገባደድ በጣት የሚቆጠሩ ጨዋታዎች ቀርተዋል። ለከርሞ ዓመት በሊጉ ለመጫወት ዕድሉ እጅግ የጠበበበት ኤሌክትሪክ በመጣበት ዓመት ወደ ታችኛው ሊግ መውረዱን ምናልባት ነገ ሊያረጋግጥ ይችላል። በዚህም ቡድኑ ነገ ከሦስት ነጥብ ጋር የማይገናኝ ከሆነ እንደ ለገጣፎ 5 ጨዋታዎች እየቀሩት መውረዱ ሊረጋገጥ ይችላል። የሆነው ሆኖ ዕድሉ ቢጠብም ከናፈቀው ድል ጋር ታርቆ የመጨረሻ መጨረሻ ተጋድሎ ለማድረግ ጠንካራ ፉክክር እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
\"\"

ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በሲዳማ ቡና አንድ ለምንም የተረታው መቻል ዳግም ወደ ድል ተመልሶ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጠውን ሦስት ነጥብ ለማግኘት ብርቱ ትግል እንደሚያደርግ ይታመናል። በጥሩ ብቃት ላይ ይገኝ የሚመስለው ቡድኑ ሦስት ነጥብ ባስረከበበት ጨዋታ በተለይ በማጥቃቱ ረገድ የነበረው ውስንነት ዳግም አገርሽቶ ነበር። እርግጥ ይህ የጎል ፊት አይናፋርነት ዓመቱን ሙሉ ቡድኑን እንዲቸገር ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም የነገ ተጋጣሚው ኤሌክትሪክ ደካማ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ክለብ ስለሆነ እምብዛም ላይቸገር ይችላል።

የቡድን ዜናን በተመለከተ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ያለውን ወቅታዊ መረጃ ማግኘት ባንችልም በመቻል በኩል ከውድድር ዓመቱ ውጪ ከሆነው ፍፁም ዓለሙ እና ልምምድ ከጀመረው ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ውጪ ሁሉም ተጫዋቾች ለፍልሚያው ዝግጁ እንደሆኑ ታውቋል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሃያ ሰባት (27) ጊዜ ተገናኝተው ኤሌክትሪክ አሥር (10) በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን መቻል አምስት (5) አሸንፎ በ አሥራ ሁለት (12) ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። መቻል ሃያ ዘጠኝ (29) ሲያስቆጥር ኤሌክትሪክ ደግሞ አርባ (40) ግቦች አሉት።