ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን ባረጋገጠበት ጨዋታ ከመቻል ጋር ነጥብ ተጋርቷል

ሁለቱን የመዲናይቱ ክለቦች ያገናኘው ጨዋታ 2ለ2 ሲጠናቀቅ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በመጣበት ዓመት ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን መውረዱ ተረጋግጧል።

ሽንፈት አስተናግደው በዛሬው ጨዋታ የተገናኙት ሁለቱ ክለቦች በተመሳሳይ የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። ኤሌክትሪክ አማረ በቀለ ፣ ስንታየሁ ዋለጪ እና ፍፁም ገብረማርያምን በማታይ ሉል ፣ ሔኖክ አንጃው እና አብዱራህማን ሙባረክ መቻሎች በበኩላቸው በሀይሉ ሀይለማርያም ፣ በሀይሉ ግርማ እና እስራኤል እሸቱን በዳዊት ማሞ ፣ ተሾመ በላቸው እና ምንይሉ ወንድሙ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

\"\"

ጨዋታው ፈጣን ሙከራን በኤሌክትሪክ በኩል በማድረገ ነበር የጀመረው ፤ ገና ከጅምሩ አብነት ደምሴ ከረጅም ርቀት የደረሰውን ኳስ በቀላሉ ከመረብ አሳረፈው ተብሎ ሲጠበቅ ውብሸት ጭላሎን አሳቅፎታል። ኳስን በራሳቸው እግር ስር በማቆየት ወደ መስመር በመጣል የኤሌክትሪክ የግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት መቻሎች ደቂቃው ብዙም ሳይጓዝ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። መነሻዋን መሐል ሜዳ አድርጋ አህመድ ረሺድ ጋር ደርሳ በመጨረሻም ሳሙኤል ሳሊሶ ወደ ጎል ሲያሻማ ተሾመ በላቸው የተከላካዮች የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ጎል አድርጓታል።


የተጋጣሚያቸውን ተቋራጭ ኳስ ቅብብል በሚያገኙበት ወቅት አብዱራህማን ሙባረክን ባነጣጠረ እንቅስቃሴ ይጫወቱ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ከሚታይባቸው ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ አኳያ የመቻልን የተከላካይ ክፍል ለመስበር ባይታደሉም ሁለት አጋጣሚን አግኝተው ነበር። አብዱራህማን ሙባረክ በተከታታይ ሁለት ጊዜ ከግብ ጠባቂው ውብሸት ጋር ተገናኝቶ የግብ ዘቡ ሳይቸገር የያዘበት ኳስ ተጠቃሾቹ ናቸው። በጨዋታው ብልጫን መቻሎች ወስደው ቶሎ ቶሎ ሳይቸገሩ በወጥነት የኤሌክትሪክ የግብ ክልል በተለይ በመስመር አጨዋወት ሲደርሱ ቢስተዋልም አጨራረስ ላይ ኮስታሮች አልነበሩም። አህመድ ረሺድ ወደ ግብ ክልል ልኮ ብረት ከመለሰበት እና 33ኛው ደቂቃ ላይ ከነዐን ማርክነህ ላይ በተሰራ ጥፋት ሳሙኤል ሳሊሶ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው ካክፓ ከመለሰበት ሙከራ በኋላ ብዙም ፉክክሮች ያልነበሩት አጋማሹ በመቻል 1ለ0 ተገባዷል።


ከዕረፍት ተመልሶ ጨዋታው ሲቀጥል ኤሌክትሪኮች መሐል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ ሽፋን ለመስጠት የሚመስል ለውጥ ፀጋ ደርቤን በስንታየው ዋለጪ ሲተኩ ጉዳት ያስተናገደው ታፈሰ ሰርካን በጌቱ ሀይለማርያም ለውጠዋል። ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ መቻሎች ጨዋታውን ከጀመሩ በኋላ ከቆመ ኳስ እና ከተሻጋሪ ኳሶች በግንባር ሊቆጠሩ የሚችሉ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተመልክተናል። ለዚህም ማሳያው ከተደጋጋሚ ኳሶች በኋላ 52ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሜዳው ክፍል ሳሙኤል ሳሊሶ በረጅሙ አሻግሮ ምንተስኖት አዳነ ሞክሯት ብረቱ ሲመልሰው ዳግም ሳሙኤል እግሩ ስር ገብታ የመታትን ኳስ ካክፓ እንደምንም አውጥቶበታል። በሒደት የነበረባቸውን ደካማ የጨዋታ መንገድ በማረም ኳስ ይዘው በመጫወት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ለመድረስ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት ኤሌክትሪኮች ወደ አቻ ውጤት መጥተዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ አብዱራህማን ሙባረክ ከመሐል ሜዳ የደረሰውን ኳስ ወደ ሳጥኑ እየገፋ ጠርዙ ላይ እንደደረሰ አክርሮ ወደ ጎል ሲመታ የውብሸት ጭላሎ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታክሎበት ወደ ጎልነት ቀይሯታል።


እስራኤል እሸቱን በማስገባት የአጥቂ ቁጥራቸውን ጉልበት ለመስጠት አስበው የነበሩት መቻሎች በሳሙኤል ሳሊሶ የርቀት እንዲሁም ከቆመ ኳስ ግብ ፍለጋ ላይ ቢሰማሩም በተቃራኒው ጥሩ እየሆኑ የመጡት ኤሌክትሪኮች ሁለተኛ ግብ አክለዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ከድር ኢብራሂም ከቀኝ ወደ ውስጥ ሲያሻማ የግብ ጠባቂው ውብሸት መዘናጋት ተጨምሮበት አብዱራህማን ሙባረክ ለራሱ እና ለቡድኑ የግብ መጠኑን ሁለት አድርጓል።

\"\"

ከመሪነት ወደ ተመሪነት ከመጡ በኋላ ወደ አቻነት ለመምጣት ተደጋጋሚ ጥረት ያደረጉት መቻሎች ግርማ ዲሳሳ የማታይ ሉልን ስህተት ተጠቅሞ ከግቡ ጋር ቢገናኝም ሳይታሰብ ወደ ላይ ሰዷታል። በዚህች ኳስ የተበሳጨው የኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ካክፓ ቸሪፍ ዲን የቡድን አጋሩ ማታይን ገፍትሮ የጣለበት ቅፅበት አስገራሚ ሁነት ነበረች። መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው እስራኤል እሸቱ ከሳጥን ውጪ ማራኪ ጎል አስቆጥሮ በመጨረሻም ጨዋታው 2ለ2 ተቋጭቷል። ውጤቱን ተከትሎ ኤሌክትሪክ በመጣበት ዓመት ቀሪ አምስት ጨዋታዎች እየቀሩት ለመውረድ ተገዷል።