\”በመውረዳችን በጣም አዝኛለው\” ስምዖን አባይ
\”አቻ መጠናቀቁ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም ፤ ሦስት ነጥብ ይገባን ነበር\” ፋሲል ተካልኝ
ኢትዮ ኤሌክትሪክ መውረዱን ባረጋገጠበት እና ሁለት አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ የሰጡት አስተያየት እንደሚከተለው ቀርቧል።
ስምዖን አባይ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ስለ ጨዋታው…
በእንደዚ አይነት ጭንቀት ሆነን ከመጀመሪያው ጀምሮ የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገናል። በመጀመርያው አጋማሽ የትኩረት ማነስ ነበር ፤ ጎሉ ሲቆጠርብንም ተጫዋቾች ከኋላ እያደረግን ነበር ስንከላከል የነበረው። በሁለቱም ክንፍ የነበሩ ተከላካዮቻችም የትኩረት ማጣት ችግር ነበራቸው። ከዕረፍት መልስ ተጫዋቾች ቀይረን ችግሩን ለመቅረፍ ያደረግነው ጥረትም የተሳካ ነበር ፤ ግን እንደተለመደው ባለቀ ሰዓት ትኩረት በማጣታችን ግብ ተቆጥሮብናል ፤ ያሳዝናል።
ላለመውረድ ስላደረጉት ጥረት…
በአጠቃላይ የዓመቱ ጉዞ የተዘበራረቀ ነበር። ቡድኑን ለመደገፍ ከቦርድ ጀምሮ ጥቂት ቢሆኑም ደጋፊም መጥቶ በመደገፍ ሁሉም ጥረት አድርጓል። ሆኖም ብዙ የተዘበራረቁ ነገሮች ነበሩ እነሱን ለማስተካከል ጥረት አድርገናል ግን አልተሳካም ፤ ዛሬ በተጫዋቾቼ ደስተኛ ነኝ አልከፋኝም ብዙ ጥረቶች አድርገዋል።
ቡድኑ ስለመውረዱ…
በመውረዳችን በጣም አዝኛለው።
ዛሬ እንደነበረን እንቅስቃሴ የያዝናትን ጥቂት ጭላንጭል ተስፋ ይዘን እንቀጥላለን ብዬ አስቤ ነበር ፤ በመጨረሻ ሰዓት ግብ አስተናግደን ሁለት ነጥቦች ጥለናል። አዝናለው በጣም።
ፋሲል ተካልኝ – መቻል
ስለ ጨዋታው…
ጨዋታው ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። ብዙ የጎል ዕድሎች ፈጥረናል ግን ማስቆጠር አልቻልንም። ሁለት ጊዜ ብረት መልሶብናል። በርግጥ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ አስራ አምስት ደቂቃዎች የትኩረት ማጣት ነበረብን። በእነዛ ደቂቃዎች ነው ሁለት ግቦች ያስተናገድነው ፤ ከዛ በኋላ የተጫዋች ቅያሪ አድርገን ውጤት ለማምጣት ሞክረናል። አቻ መጠናቀቁ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም ፤ ሦስት ነጥብ ይገባን ነበር።
በጨዋታው ስለታየው የወጥነት ችግር…
እነሱ ነፃ ሆነው ነበር የተጫወቱት። በመጀመርያዎች ሀያ ደቂቃዎች ጨዋታውን መግደል ነበረብን ፤ ብዙ የግብ ዕድሎች ፈጥረና አስቆጥረን ጨዋታውን መቆጣጠር ነበረብን። ሁለት ለአንድ ከተመራን በኋላም የግብ ዕድሎች ፈጥረናል። ጨዋታውን ማሸነፍ ይገባን ነበር ፤ ግን አልተሳካም።