አርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጠንከር ያለ ቅጣት ተላልፎባቸዋል

የአርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ደጋፊዎች በፈፀሙት ያልተገባ ድርጊት ቅጣት ሲተላለፍባቸው የሳምንቱ ውሳኔዎችም ተያይዘው ወጥተዋል።

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር እና ሥነ ስርዓት ኮሚቴ በሊጉ የ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ተንተርሶ ከዳኞች እና ከጨዋታ ታዛቢዎች የደረሰውን መረጃ ዋቢ በማድረግ በታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ በክለቦች እና ተጫዋቾች ላይ ቅጣትን ጥሏል።

\"\"

ድሬደዋ ከተማ ወልቂጤን ሲረታ ለገጣፎ ለገዳዲ በበኩሉ ከኢትዮጵያ ቡና ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ የሁለቱም ክለብ ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ከአራት በላይ ካርድ በማግኘታቸው እያንዳንዱ ክለብ የአምስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ሲጣልበት አርባ ምንጭ ከተማ ከአዳማ ጋር ያለ ጎል ባጠናቀቀው ጨዋታ ላይ የክለቡ ደጋፊዎች አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ እና የቡድን አመራሮች ላይ በሰነዘሩት አፀያፊ ስደብ የሃምሳ ሺህ የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባቸዋል።

በሌላ በኩል ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱን የጨዋታ ዳኞች አፀያፊ በመሳደባቸው ከዚህ በፊትም የክለቡ ደጋፊዎቹ አፀያፊ ስድብ በመሳደብ ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው የሰባ አምስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ተወስኗል። ከዚህም በተጨማሪ የክለቡ ደጋፊዎች ከስታድየም ቅጥር ግቢ ውጭ የፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ንብረት በሆነው ተሽከርካሪ ላይ ድንጋይ በመወርወር ጉዳት በማድረሳቸው ክለቡ የተጎዳውን ተሽከርካሪ እንዲያሰራ ወይም ባለንብረቱ አስርቶ በሚያቀርበውን ዋጋ መሰረት ክፍያ እንዲፈፅም ወስኗል ።

\"\"

በተጫዋች በኩል ያሬድ ዳዊት (ወላይታ ድቻ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀሙ ቀይ ካርድ አይቶ በመወገዱ ኤሪክ ካፓይቶ (አርባምንጭ ከተማ) ፣ ፍሪምፖንግ ሜንሱ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) ፣ ረመዳን የሱፍ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) እና ዮሴፍ ዮሀንስ (ድሬደዋ ከተማ) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ካርድ በመመልከታቸው የ1 ጨዋታ ዕገዳና በተጨማሪ አንድ ሺ አምስት መቶ ብር እንዲከፍሉ ተወስኗል።