ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 25ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የተጠናቀቀውን የ25ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎችን ተንተርሰን ነጥረው የወጡ ተጫዋቾች እና አሰልጣኝ መርጠናል።

አሰላለፍ (4-3-3)

ግብ ጠባቂ

ዳንኤል ተሾመ – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከወራጅነት ስጋት ለመላቀቅ ወልቂጤ ከተማን ባሸነፈበት ጨዋታው ግብ ጠባቂው ዳንኤል ያደረገው እንቅሰቃሴ በምርጥ ስብስባችን ውስጥ ልናካተው ችለናል። ጨዋታው እንደተጀመረ የጌታነህ ከበደ እና በአጋማሹ የአቤል ነጋሽን ኳሶች ያከሸፈበት እንዲሁም ደግሞ ቡድኑን ሲመራ ከነበረበት መንገድ አንፃር ሊመረጥ ችሏል።

ተከላካዮች

ሰይድ ሀሰን – ሀዋሳ ከተማ

በመድኑ ጨዋታ ቡድኑ ሀዋሳ ሁለት ጊዜ ሲመራ ከነበረበት ወደ አቻነት ለመሸጋገሩ የተከላካዩ ሚና ግንባር ቀደሙን ድርሻ ይወስዳል። ከተሰጠው የመከላከል ድርሻው በተጨማሪ የሀዋሳን የማጥቃት ጉልበት ከፍ በማድረግ ሁለት የግንባር ኳሶችን ያስቆጠረው ተከላካዩ የምርጫችን አካል ሆኗል።

\"\"

ጊት ጋትኩት – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና ተከታታይ አራተኛ ድሉን በእጁ ሲጨብጥ ከጨዋታ ጨዋታ ራሱን እያጎለበተ የመጣው ተከላካዩ ጊት በዋነኝነት ይጠቀሳል። የፋሲል ከነማን የሚሻገሩ ኳሶች ቀድሞ በመገኘት በመግጨት እና በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት ኳስን ሲያጥል ከነበረው እንቅስቃሴው በመነሳት ከአጣማሪው ደስታ ደሙ ንፅፅራዊ በሆነ ምርጫ ልቆ በመገኘት በምርጥነት ተካቷል።

እያሱ ለገሠ – ድሬዳዋ ከተማ

ከመውረድ ስጋት በመላቀቅ ከፍ ባለ ደረጃ ላይ ተገኝቶ ለማጠናቀቅ ይጠበቅ በነበረው ጨዋታ ተከላካዩ ከተሰጠው የኋላ ሽፋን ኃላፊነት በዘለለ በጥልቀት ተሻጋሪ ኳሶች ሲገኙ እየተሳበ የሚጫወትበት መንገድ እና ቡድኑም መሪ ሲሆን ቀዳሚዋን ግብ ማስቆጠር መቻሉ ከሔኖክ አዱኛ ጋር ተነፃፅሮ ጥሩ ጊዜን ያሳለፈ በመሆኑ መርጠነዋል።

ካሌብ በየነ – ሀድያ ሆሳዕና

ሀድያ ሆሳዕና ጭቃማ በነበረው የባህር ዳር ጨዋታ ሦስት ነጥብን ለማግኘት የዚህ ወጣት ተከላካይ ሚና ድርሻው ከፍ ያለ ነበር። ቡድኑ በርካታ ቋሚ ተሰላፊዎቹ በጉዳት እና ቅጣት ባልነበሩት ጨዋታ ለቡድኑ ውጤት ይዞ መውጣት በተለይ ከዕረፍት መልስ ያደረገው የመከላከል ወጥነት አኳያ የስብስባችን አካል ሆኗል።

አማካዮች

ግርማ በቀለ – ሀድያ ሆሳዕና

ሀድያ ሆሳዕና ባህር ዳር ከተማ ከመሪው ያለውን ነጥብ እንዳያጠብ ያደረገበት ውጤት ሲመዘገብ ለቡድኑ ሙሉውን የጨዋታ ደቂቃ ተሰልፎ በመጫወት ሲታገል የነበረው ግርማ በቀለ ድርሻ ትልቁን ቦታ ይይዛል። የባህር ዳር የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ኳስ እንዳይቀባበሉ በማስጣሉም ሆነ ከዕረፍት መልስ ተጋጣሚው ሙሉ ለሙሉ ብልጫ በወሰደበት ወቅት ከአማካይ ወደ ተከላካይ ቦታ ሽግግር በማድረግ ወደ ጎልነት እንዳይለወጡ በርካታ ኳሶችን ሲያስጥል ስለ ነበር በምርጥ 11 ተካቷል።

ሱራፌል ዳኛቸው – ፋሲል ከነማ

ሲዳማ ቡና ፋሲልን ባሸነፈበት ጨዋታው አማካዩ ቡድኑ ይሸነፍ እንጂ ሜዳ ላይ የነበረው ተጋድሎ ቀላል አልነበረም። ቡድኑ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ በወሰደበት ሰዓት ከርቀት ሙከራዎችን በማድረግ እና ለአጥቂ ተጫዋቾች ኳስን ከሚያቀርብበት ምቹ እንቅስቃሴው አንፃር ልንመርጠው ችለናል።

ሱራፌል ጌታቸው – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ወደ ድል ተጫዋቹ ወደ ቋሚ አሰላለፍ በተመለሰበት የወልቂጤ ጨዋታ አማካዩ ሜዳ ላይ ጥሩ ቆይታን አድርጎ ወጥቷል። ተቀይሮ እስከሚወጣ ድረስ የመሐል ሜዳውን አጠገቡ ካሉ ተጫዋቾች ጋር በመቆጣጠር ሲጫወት ከነበረበት እንቅስቃሴው እና የቡድኑንም ቀዳሚ ግብ ከመረብ ማሳረፉን ተንተርሶ ተመርጧል።

\"\"

አጥቂዎች

ቸርነት ጉግሳ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በተከታታይ ጨዋታዎች ጎል ማስቆጠር የቻለው ቸርነት በፈታኙ የወላይታ ድቻ ጨዋታ ላይ ምርጥ ሆኖ አሳልፏል። በመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ድቻ ላይ ለቡድኑ ጎል ያገባው እና በሁለተኛው ዙር ቡድኑ 2ለ1 ሲረታ የቀድሞው ክለቡ ላይ በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ግብን ያስገኘው ተጫዋቹ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ያሳየው ጥሩ እንቅስቃሴው አስመርጦታል።

ተመስገን ብርሀኑ – ሀድያ ሆሳዕና

ከታችኛው ቡድን አድገው ቡድናቸውን ከሚያገለግሉ ወጣቶች መካከል ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ተመስገን ይጠቀሳል። ባህር ዳር ከተማን በረቱበት ወቅት በማጥቃቱ የጎላ ድርሻ እና ግብም ጭምር አስቆጥሮ የነበረው እና በሁለተኛው አጋማሽም ወደ ኋላ መስመር ተመልሶ ቡድኑን በመከላከሉ ያገዘው ተመስገን በምርጥ 11 የአጥቂ ቦታ ላይ መርጠነዋል።

አብዱራህማን ሙባረክ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ኢትዮ ኤሌክትሪክ መውረዱን ባረጋገጠበት የመቻሉ ጨዋታ ላይ ከመመራት ተነስቶ ቡድኑ መርቶ በመጨረሻም አቻ ውጤትን ሲያስመዘግብ አጥቂው ምንም እንኳን ቡድኑ በድል ሳይታጀብ ቢወርድም ሜዳ ላይ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በብርቱ በመታገል ሁለት ጎሎችንም ጭምር ማስቆጠሩ ሊካተት ችሏል።

አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ሀድያ ሆሳዕና

ወደ ሰባት የሚደርሱ ቋሚ ተሰላፊዎችን በጉዳት እና ቅጣት ሀድያ ሆሳዕና ባጣበት የባህር ዳሩ ጨዋታ በበርካታ ወጣቶች ታግዘው በመግባት ቡድኑ ሦስት ነጥብን ይዞ እንዲወጣ ማድረግ ችለዋል። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ውጤቱን ለማስጠበቅ ቡድኑ በጥብቅ መከላከል ሙሉ ነጥቡን እንዲይዝ ማድረጋቸው ከአሰልጣኝ አስራት አባተ እና ዘሪሁን ሸንገታ ጋር ተወዳድረው በመላቃቸው በምርጥ የሳምንቱ አሰልጣኝ ቦታ ላይ ሊመረጡ ችለዋል።

ተጠባባቂዎች

ሚካኤል ሳማኪ
እንየው ካሳሁን
ደስታ ደሙ
ሳሙኤል ሳሊሶ
ሰመረ ሀፍታይ
ሲሞን ፒተር
አማኑኤል አረቦ

\"\"