26ኛው የጨዋታ ሳምንት ነገ ሲጀምር የሚከናወኑትን ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እነሆ !
ለገጣፎ ለገዳዲ ከ አዳማ ከተማ
መውረዱን ካረጋገጠው ለገጣፎ ለገዳዲ ይልቅ ደረጃውን ለማሻሻል እና ከመጨረሻ ሳምንታት ትንቅንቆች ለመራቅ ተጨማሪ ነጥቦችን ለሚፈልገው አዳማ ከተማ ትርጉም የሚኖረው ይህ ጨዋታ 09:00 ላይ ይጀምራል።
በመጣበት ዓመት ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን ያረጋገጠው ለገጣፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ ውስን መሻሻሎች እያሳየ ቢመጣም ከመውረድ መትረፍ አልቻለም። በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች በአንፃራዊነት የተሻለ የማጥቃት አጨዋወት የነበረው ቡድኑ ለግል ስህተቶች ቅርብ የሆነ ተከላካይ ክፍል አለው። በነገው ዕለት ይህ ችግር መቅረፍም በጨዋታው የተሻለ ነገር እንዲያሳይ ያግዘዋል ተብሎ ይታመናል።
ኳስን የሚቆጣጠር ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል የሚሄድ ቡድን የሰሩት አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሥስት ነጥብ ማግኘት አልቻሉም። የነገው ጨዋታ ማሸነፍ ካልቻሉም በሰባት ነጥብ ከራቁት ያለመውረድ ትግል ውስጥ እንዳይካተቱ ጥንቃቄ የተሞላበት የማጥቃት አጨዋወት ይተገብራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለወትሮ ስል የአጥቂ ክፍል የነበራቸው አዳማዎች ባለፉት ሥስት ጨዋታዎች ያስቆጠሩት የግብ መጠን አንድ መሆኑ ሲታይ ደግሞ የአጥቂ ክፍሉ መዳከም ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በነገው ጨዋታም ይህንን ችግር መቅረፍ አሸናፊ ከሚያደርጋቸው መመዘኛዎች አንዱ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል።
በጨዋታው አዳማ ከተማ ጀሚል ያዕቆብን በጉዳት ሲያጣ ለወራት ከሜዳ ርቆ የቆየው ዳዋ ሆቴሳ እንደሚመለስለት ተሰምቷል። በለገጣፎ ለገዳዲ በኩል ሱራፌል ዐወል በቅጣት ሱሌይማን ትራኦሬ ደግሞ በጉዳት ጨዋታው ሲያልፋቸው በረከት ተሰማ እና አስናቀ ተስፋዬ ደግሞ ከጉዳት ተመልሰዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ የተገናኙበትን ጨዋታ አዳማ ከተማ 3-0 ማሸነፍ ችሎ ነበር።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ባህር ዳር ከተማ
በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ወሳኝ ጠቋሚ ነጥብ ይገኝበታል ተብሎ የሚገመተው ፈረሰኞቹ እና የጣና ሞገዶቹን የሚያገናኘው ጨዋታ ከነጥብ ቅርርቡ እና የዋንጫ ፉክክሩ በተጨማሪ ማራኪ የሜዳ ላይ ፍልሚያ ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ባሳለፍነው ሳምንት በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት አስተናግደው ከመሪው ጋር ያላቸው የነጥብ ልዩነት ማስጠበቅ ያልቻሉት የጣና ሞገዶቹ በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ለመቆየት የነገው ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።
ከተከታታይ ድሎች በኋላ ሽንፈት አስተናግደው ወደ ተጠባቂው ጨዋታ የሚያመሩት ባህር ዳሮች በነገው ጨዋታ የአማካይ ክፍል ብልጫ ለመውሰድ ይቸገራሉ ተብሎ ባይታሰብም የተጋጣሚን ዋነኛ የማጥቅያ መንገድ የሆነው የመስመር አጨዋወት እና ቀጥተኛ ኳሶች በመከላከል የተሻለ ቀን ማሳለፍ ግድ ይላቸዋል። ሁለቱም የመስመር ተከላካዮቻቸው በማጥቃቱ ላይ የሚያሳትፍ አጨዋወት ያላቸው አሰልጣኝ ደግአረግ በነገው ዕለት ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይገመትም። ሆኖም ኳስ ለመቆጣጠር የማይሰንፈው የቡድኑ አማካይ ክፍል በተለመደው ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ላይ ጥሩ የማጥቃት አስተዋፅዖ አበርክቶ ክፍተቱን ይደፍናል ተብሎ ይታመናል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአንድ ጨዋታ ብቻ ግብ ሳያስተናግድ የወጣው እና በተጠቀሱት ጨዋታዎች በጨዋታ 1.4 ግቦችን ያስተናገደው የተከላካይ ክፍልም የነገው ተጋጣሚው ሰፊ የማጥቃት አማራጭ ያለው ቡድን እንደመሆኑ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።
በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሎ በዋንጫ ፉክክሩ ላይ መቀዛቀዝ አሳይቶ የነበረው ጊዮርጊስ የመጨረሻው ሳምንት ጨዋታ አሸንፎ ወደዚህ ጨዋታ መቅረቡ በሥነ-ልቦና ረገድ እንደሚያግዘው እሙን ነው።
ኳስ ለመቆጣጠር አመቺ የሆነ የአማካይ ክፍል ቢኖራቸውም በአብዛኛው ጊዜ ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የማይሰጡት አሰልጣኝ ዘሪሁን በነገው ጨዋታም ከተለመደው ቀጥተኛ እና የመስመር አጨዋወት ወጣ ያለ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ሌላው ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች የማጥቃት አጨዋወታቸው ተገማች እየሆነ በመምጣቱ መጠነኛ ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ ይታሰባል። በርግጥ ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች ያስቆጥር እንጂ በጥራታቸው ላቅ ያሉ የማጥቃት ባህሪ ላለው ቡድን ይህ ቁጥር ጥቂት ነው። እንዲህም ሆኖ በርካታ የግብ ምንጭ ያለው ቡድኑ ለተጋጣሚ ተከላካዮች ፈተና እንደሚሆን መገመት ግን አይከብድም። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ ያልወጣው የተከላካይ ክፍሉም የነገው ተጋጣሚው ግቦች ለማስቆጠር የማይሰንፈው ባህርዳር እንደመሆኑ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።
ባህር ዳር ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ጉዳት ገጥሞት ተቀይሮ ወጥቶ የነበረው ፉዓድ ፈረጃ የሚመለስለት ሲሆን ቀሪው ስብስብም ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆኖ ለወሳኙ ጨዋታ ይደርሳል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ ፍሪፖንግ ሜንሱ እና ረመዳን የሱፍ በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት የማይኖሩ ሲሆን አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ምኞት ደበበ ልምምድ የጀመሩ ቢሆንም ለነገው ጨዋታው ዝግጁ መሆናቸው አጠራጣሪ ነው። በሌላ በኩል ጋቶች ፓኖም እና ሱሌማን ሀሚድ ባለፈው ሳምንት በተጠባባቂ ወንበር ላይ የነበሩ በመሆኑ አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚችሉ ይገመታል።
የሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ ሰባት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ሁለት ሁለት ጊዜ ተሸናንፈው ሦስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ቅዱስ ጊዮርጊስ ስድስት ባህር ዳር ከተማ አራት ግቦችን አስቆጥረዋል።