ሪፖርት | አማኑኤል አረቦ በሽርፍራፊ ሰከንድ ለገጣፎን ድል አቀዳጅቷል

ለተመልካች ሳቢ ባልነበረው የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ከሊጉ የወረደው ለገጣፎ ለገዳዲ አዳማ ከተማን 1ለ0 ረቷል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ የተጋራበትን አሰላለፍ ዛሬም ይዞ ሲገባ ከአርባምንጭ ከተማ የአቻ ውጤት አንፃር አዳማ ከተማ በአራቱ ላይ ለውጥን አድርጓል። ጀሚል ያዕቆብ ፣ አድናን ረሻድ ፣ ዮሴፍ ታረቀኝ እና ነቢል ኑሪን በአቡበከር ወንድሙ ፣ አማኑኤል ጎበና ቢኒያም አይተን እና ከረጅም ጉዳት በኋላ የተመለሰው ዳዋ ሆቴሳን በቋሚነት ተጠቅመዋል።

\"\"

እጅግ አሰልቺ መልክ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያው አጋማሽ ጨዋታው በተጀመረ ገና 2ኛው ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች በሽግግር የጨዋታ መንገድ ቦና ዓሊ ወደ ጎል መቶ ኮፊ ሜንሳህ ከያዘበት አጋጣሚ ውጪ የጨዋታው ቀሪ ደቂቃዎች በሙሉ መሐል ሜዳ ላይ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውጪ አይናፋርነቱ ጎልቶ የታየበት ነበር ማለት ይቻላል።


አዳማ ከተማዎች በንፅፅር ኳስን ከራሳቸው ሜዳ አመዛኙን ጊዜ እየገፉ በመውጣት ጥቃትን ለመሰንዘር የሞከሩበት ለገጣፎ ለገዳዲወች በረጃጅም ኳሶች ሁለቱን አጥቂዎች ኢብሳ እና መሐመድን ባነጣጠረ መልኩ ለመጫወት ቢጥሩም ፍፁም የተቀዛቀዘ ቅርፅን የተላበሰው ጨዋታ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል በ0ለ0 ውጤት አምርቷል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽም ቡድኖቹ አሁንም ሜዳ ላይ ከሚያሳዩት የኳስ ማንሸራሸር ሒደት ውጪ የጠሩ ዕድሎች ፈጥረዋል ለማለት አይቻልም። ለገጣፎዎች አጋማሹ በተጀመረ ከአንድ ደቂቃ ቆይታ መልስ አማካዩ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ የሰጠውን ኳስ ኢብሳ በፍቃዱ በሚያስቆጭ መልኩ ሳይጠቀምባት ቀርቷል። ካለፉት የጨዋታ እንቅስቃሴዎቻቸው በተገደበ መልኩ ረጅሙን ደቂቃ መሐል ሜዳ ለማሳለፍ የተገደዱት ቡድኖች የተለየ ነገር ለማየት ጨዋታው ያስቻለን ከ65 ደቂቃዎች በኋላ ነበር።


ቦና እና ቢኒያምን አስወጥተው ዮሴፍ እና አሜን ወደ ሜዳ ያስገቡት አዳማዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የጨዋታ ፍሰት ዮሴፍ ታረቀኝ ከመስዑድ በተቀበለው ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ኮፊ ሜንሳህ ሳይቸገር ይዞበታል። የመጨረሻዎቹን የጨዋታ አስር ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት አዳማዎች በዮሴፍ ታረቀኝ የቅጣት ምት ተጨማሪ ሙከራን አድርገው ኮፊ ሜንሳህ ዳግም ይዞበታል። ጨዋታው ከነበረው የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ አንፃር ያለ ጎል ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ በጭማሪ ሽርፍራፊ ሰከንድ አማኑኤል አረቦ በመልሶ ማጥቃት ለገጣፎን አሸናፊ ያደረገች ግብን አስቆጥሮ ጨዋታው 1ለ0 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።