ሪፖርት | በጭማሪ ሽርፍራፊ ሰከንድ ጎል መቻል ከሀዋሳ ጋር ነጥብ ተጋርቷል

የመጨረሻ ደቂቃ ትዕይንቶች በበዙበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ከመቻል ጋር 1ለ1 አጠናቋል።

መቻል ከኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አስፈልጎታል። ከነዐን ማርክነህ እና ምንይሉ ወንድሙን በግርማ ዲሳሳ እና እስራኤል እሸቱ ሲተኩ ከመድኑ የአቻ ውጤት አንፃር ሀዋሳዎች በአምስቱ ላይ ቅያሪ ማድረግ ችለዋል። አቤኔዘር ኦቴ ፣ ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ ዳዊት ታደሰ ፣ አዲሱ አቱላ እና እዮብ አለማየሁን በሰለሞን ወዴሳ ፣ በረከት ሳሙኤል ፣ በቃሉ ገነነ ፣ ሙጂብ ቃሲም እና ዓሊ ሱለይማን ተተክተዋል።

\"\"

ጥሩ የፉክክር እንቅስቃሴዎችን ገና ከጅምሩ ያስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ግለቱ ከፍ ያለ በሽግግር እና በመስመር የጨዋታ አቀራረብ ለመጫወት የሞከሩበትን መንገድ አስተውለናል። ፈጠን ባለ ቅብብሎች የጀመረው ጨዋታ 4ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ነበር ሙከራን ያሳየን በዚህም ከቀኝ የሜዳው ክፍል ዓሊ ሱለይማን ወደ ውስጥ ሲያሻግር ሙጂብ ቃሲም ከግቡ ጋር ተገናኝቶ ውብሸት ጭላሎ አስጥሎታል። በሁለት መስመሮች በኩል ከግርማ እና ሳሙኤል በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች እስራኤልን እሸቱን ባማከለ አጨዋወት ለመጫወት የጣሩት መቻሎች 7ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ዳዊት ወርቁ መሐመድ ሙንታሪን የፈተነች ሙከራን አድርጎ ነበር።

የግብ አጋጣሚን ለመፍጠር ከሀዋሳ በተሻለ የግብ ክልል የሚደርሱት መቻሎች 17ኛው ደቂቃ ለግብ ተቃርበው ነበር መድሀኔ ብርሀኔ በተሳሳተበት ቅፅበት ግርማ ዲሳሳ ወደ ጎል ሞክሮ አሁንም ሙንታሪ አውጥቷታል። ከዚህች ሙከራ ሁለት ደቂቃ ቆይታ መልስ ሳሙኤል ሳሊሶ ያቀበለውን እስራኤል በቀጥታ መቶ ሙንታሪ ለሦስተኛ ጊዜ አድኖታል። ወደ ግራ የመቻል የሜዳ ክፍል አዘንብለው የዓሊን ፍጥነት በመጠቀም ዕድሎችን ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ሀዋሳዎች በተጫዋቹ የተደረጉ ሁለት ሙከራዎi- ብቻ ይወሳሉ። የመስመር አጨዋወትን ያጠናከሩት መቻሎች 25ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ከግሩም ያገኘውን መቶ ሙንታሪ የመለሰበት በሀዋሳዎች በኩል 37ኛ ደቂቃ ዓሊ ከቅጣት ምት በውብሸት ከወጣበት ሙከራ በኋላ አጋማሹ በ0ለ0 ተገባዷል።

ጨዋታው ከዕረፍት እንደተመለሰ አንድ ደቂቃ ብቻ እንደተቆጠረ ግብ ተስተናግዶበታል። 46ኛው ደቂቃ ላይ በቅብብል ወደ መስመር የደረሱት ሀዋሳዎች ሙጂብ እና ሰይድ ተቀባብለው ሰይድ ያሻማትን ተባረክ ሄፋሞ የመቻል ተከላካዮች የአቋምም ስህተትን ተጠቅሞ በግንባር ተጭቶ ኳሷን ከመረብ አዋህዷታል። መቻሎች ምላሽ ለመስጠት በሚመስል መልኩ አደገኛ ሙከራን ከደቂቃ በኋላ ሰንዝረዋል ከቀኝ የሀዋሳ የሜዳ ክፍል ሳሙኤል ሳሊሶ አክርሮ የመታትን ኳስ ሙንታሪ ከተጫዋቾች ታግሎ ወደ ውጪ አውጥቶበታል።

\"\"

ጎል ካገኙ በኋላ አብዛኛውን ጥንቃቄ አዘል የጨዋታ መንገድን መርጠው ለኋላ መስመራቸው ትኩረት ሰጥተው የተንቀሳቀሱት ሀዋሳዎች በጥልቀት አልያም ከመስመር የሚነሱ የመቻልን ተሻጋሪ ኳሶች በመጠበቁ ተጠምደው ውለዋል። በዚህም መድሀኔ ብርሀኔ ከግራ ወደ ውስጥ አሻምቶ በተከላካዩ ዳዊት ሲመለስ ኤፍሬም በቀላሉ አምክኗታል። መቻሎች ተጨማሪ የአጥቂ እና የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ በማስገባት ወደ አቻነት ለመምጣት ታግለዋል። ሳሙኤል ሳሊሶ ከቅጣት አሻምቶ ግሩም በግንባር ገጭቶ ሙንታሪ የያዘበት እና ግርማ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ሙንታሪ ያዳነበት ከነዐን የምታስቆጭ አጋጣሚን ወደ ላይ የሰደደበት ትጠቀሳለች።

መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው የጭማሪ ደቂቃ ላይ ከዖደለቱ ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ጋር ጀምር አትጀምር በሚል በተደጋጋሚ ጭቅጭቅ ውስጥ የገባው መሐመድ ሙንታሪ በቀይ ካርድ ከሜዳ ከወጣ በኋላ ባሉት ደቂቃዎች ሀዋሳዎች ቅያሪ በመጨረሳቸው ሙጂብ ቃሲም በግብ ጠቢቀነት አገልግሏል። ጨዋታውም ሊጠናቀቅ በመጨረሻዎቹ የጭማሪ ደቂቃዎች በረከት ደስታ ከቀኝ ወደ ጎል ያሻማውን እስራኤል ነክቷት በመጨረሻ ንክኪ ምንተስኖት አዳነ የሙጂብ ቃሲምን ስህተት ተከትሎ ጎል አድርጓታል። ከጎሏ በኋላ ሀዋሳዎች በዕለቱ ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ ላይ ከፍተኛ ቅሬታን ካሰሙ በኋላ ጨዋታው 1ለ1 ተጠናቋል።