ሪፖርት | አርባምንጭ ከተማ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቋል

በአዲሱ ጊዜያዊ አሰልጣኙ እየተመራ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው አርባምንጭ ከተማ ከሊጉ የወረደውን ኢትዮ ኤሌክትሪክን 4-0 በማሸነፍ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን አለምልሟል።

አርባምንጭ ከተማ ከአዳማው የአቻ ውጤቱ የአራት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርጓል። ሱራፌል ዳንኤል ፣ አበበ ጥላሁን ፣ አቡበከር ሻሚል እና ኤሪክ ካፓይቶን ቡታቃ ሸመና ፣ አሸናፊ ኤልያስ ፣ መላኩ ኤልያስ እና አህመድ ሁሴን ሲጠቀሙ ከመቻል ነጥብ የተጋሩት ኤሌክትሪኮች በአንፃሩ ታፈሰ ሰርካን በጌቱ ኃይለማርያም ፣ ሚኪያስ መኮንን በስንታየሁ ዋልጪ ለውጠው ተጠቅመዋል።

\"\"

የአርባምንጭ ከተማ አንፃራዊ የጨዋታ የበላይነት በተስተዋለበት የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ በንፅፅር በፈጣን የጨዋታ ሽግግር ጎል ጋር በመድረሱ ቡድኑ ከተጋጣሚው የላቀ ነበር። ኤሌክትሪኮች የአርባምንጭን የስህተት ኳሶች በሚያገኙበት ወቅት ወደ ጎል ለመለወጥ ጥረት ያደረጉት ገና 6ኛው ደቂቃ ላይ ነበር በዚህም አብዱራህማን ሙባረክ ከግብ ጠባቂው ይስሀቅ ጋር አንድ ለአንጅ ተገናኝቶ በግብ ጠባቂው ቅልጥፍና የመከነችበት ትጠቀሳለች። የጨዋታ እንቅስቃሴያቸውን በይበልጥ ወደ መስመር በማድላት የጥቃት ግለቱን ከፍ ያደረጉት አርባምንጮች በተመስገን ደረሰ ባደረጉት ሙከራ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል መዳረሻቸው አድርገዋል። ኳስን ከኋላ መስርተው በሒደት ለመጫወት ቢሞክሩም ወደ አርባምንጭ የሜዳ ክልል ለመግባት ይቸገሩ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ባደረጉት የፈጣን ሽግግር ጎል ወደ ማስቆጠሩ መጥተዋል።

አሸናፊ ኤልያስን ከቀኝ በማስነሳት ወደ ተመስገን አህመድ ኳስን በመጣል ጥረቶችን ማድረግ የጀመሩት አዞዎቹ 25ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ቡታቃ ሻመና ሲያሻማ ተከላካዩ አሸናፊ ፊዳ በግንባር ገጭቶ ከመረብ በማገናኘት አርባምንጭን መሪ አድርጓል። ያሬድ የማነ በቀጥታ መቶ ይስሀቅ ተገኝ አምልጣው ወደ ውጪ ካወጣት ሙከራ መልስ በአሸናፊ ኤልያስ ተጨማሪ ሙከራን አድርገው የነበረው አርባምንጮች 37ኛው ደቂቃ እንደደረሰ በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ አሸናፊ ኤልያስ ወደ ሳጥን ደርሶ መሬት ለመሬት የላካት ኳስን አህመድ ሁሴን አመቻችቶለት እንዳልካቸው መስፍን ማራኪ ጎልን ካስቆጠረ በኋላ አጋማሹ በ2-0 ውጤት ተገባዷል።

\"\"

ከዕረፍት ጨዋታው ተመልሶ ሲቀጥል ተመጣጣኝ እንቅሰቃሴዎች የተዘወተሩበት የተቀዛቀዙ ሙከራዎች የታዩበት ሒደት አስተውለናል። ቡድኖቹ ኳስን ሲይዙ ከሚያደርጉት ማንሸራሸር ውጪ ጥራት ያላቸውን ዕድሎች በመፍጠሩ ደካማ በነበሩበት የጨዋታ አጋማሽ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ጨዋታ ቅኝት ለመመለስ ተሻጋሪ ኳሶች ላይ በይበልጥ ትኩረት ሲያደርጉ አርባምንጮች በበኩላቸው ከኋላ የሜዳው ክፍል መስርቶ በመውጣት ከዛም አጋጣሚን ካገኙ ግን ወደ ጎልነት ለመለወጥ በተለይ አሸናፊ ኤልያስን ባማከለ ፈጣን ኳሶች ለመጫወት ታትረዋል።

በዚህም አሸናፊ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ሙከራን አድርጎ በሁለተኛው አጋጣሚው የግል ጥረቱን ተጠቅሞ 79ኛው ደቂቃ ላይ አክርሮ የመታት ኳስ ከግቡ ቋሚ ጋር ተነካክታ የአርባምንጭን የጎል መጠን ወደ ሦስት ያሳደገች ጎል ሆናለች። በብዙ ረገድ ከመጀመሪያው አጋማሽ የወረደ እንቅስቃሴዎች በበረከቱበት አጋማሽ በመጨረሻ አስር ደቂቃ አርባምንጮች ባደረጉት ትጋት አራተኛ ጎል አስቆጥረዋል። በጭማሪ 90+2 ላይ እንዳልካቸው መስፍንን መነሻ ያደረገች ኳስ በአሸናፊ ኤልያስ ከመረብ አርፋለች። ከደቂቃ መልስ በበላይ ገዛኸኝ አማካኝነት አምስተኛ ልትሆን የምትችል አጋጣሚን ቡድኑ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም ካክፓ መልሶበት ጨዋታው በአርባምንጭ 4ለ0 ድል አድራጊነት ተቋጭቷል። ቡድኑም ለጊዜው ወልቂጤ እስኪጫወት ድረስ በግብ ክፍያ በልጦ ከወራጅ ቀጠናው ከፍ ብሏል።