የአሰልጣኞች አስተያየት| አርባምንጭ ከተማ 4 – 0 ኤሌክትሪክ

\”በርግጠኝነት ሊጉ ላይ እንቆያለን\” አሰልጣኝ በረከት ደሙ

\”እግርኳስ የሚጠይቀውን ነገር ማድረግ ካልቻልክ እንደዚህ ዓይነት ሽንፈት ያጋጥምሀል\” አሰልጣኝ ስምዖን አባይ

አሰልጣኝ በረከት ደሙ በመጀመርያ ጨዋታቸው ጣፋጭ ድል አስመዝግበው ኤሌክትሪክን ከረመረሙበት ጨዋታ በኋላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ በረከት ደሙ

ስለ ጨዋታው…

ጨዋታው ጥሩ ነበር፤ ያለንበት ደረጃ የሚመጥነን አይደለም። የነበረን ብቸኛ አማራጭ አጥቅቶ በመጫወት አሸንፎ መውጣት ነበር እሱን ነው ያደረግነው። አጥቅቶ በመጫወት ሦስት ነጥብ ከማግኘትም በላይ የጎል ዕዳችን ለማወራረድ ሞክረናል።

\"\"

ተጋጣሚያቸው ከጫና ውጪ ሆኖ ስለመጫወቱ…

አዎ ፤ የትናንቱ ጨዋታ ጥሩ ምሳሌ ነበር።
ቡድኑ ቢወርድም ተጫዋቾቹ ከጫና ውጭ ሆነው ራሳቸውን ለማሳየት ስለሚጫወቱ ብቃታቸው ይጨምራል። የኤሌክትሪክ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች አይቻለው፤ ዛሬ በተሻለ ተንቀሳቅሰዋል ቡድናችን በሁሉም ረገድ የተሻለ ስለነበር ግን ማሸነፍ ችለናል።

በሊጉ እንቆያለን ብለው ስለማሰባቸው…

አዎ በሚገባ፤ ቀሪ ጨዋታዋቻችን የፍፃሜ ያህል ነው የምንቆጥራቸው። ሊጉ ላይ ለመቆየት እስከ መጨረሻው የምንችለው ነገር እናደርጋለን። በዚህ መንገድ ተጫውተን ማሸነፍ ከቻልን ሊጉ ላይ የማንቆይበት ምክንያት የለም። ስብስባችን ጥሩ አቅም አለው ይህንን ነገር ሜዳ ላይ ደጋግመን የምናሳይ ከሆነ በርግጠኘነት ሊጉ ላይ እንቆያለን።

አሰልጣኝ ስምዖን አባይ

ስለ ጨዋታው…

እግርኳስ የሚጠይቀው ነገር ማድረግ ካልቻልክ እንደዚህ ዓይነት ሽንፈት ያጋጥምሀል። ሁል ጊዜ በአንድ ዓይነት የአየር ሁኔታ ወይም ሜዳ አትጫወትም። የአካል ብቃት የሚጠይቅ ከሆነ ልታሟላ ይገባል፤ የማይጠይቅ ከሆነ ደግሞ ሌላ ነገር ይዘህ ትገባለህ። ሜዳው ብቁ የአካል ብቃት ይጠይቃል፤ ኳስ ለመንሸራሸር አይመችም። ተጫዋቾቼ ግን ይህንን የተገነዘቡት አይመስለኝም። ከጨዋታው በፊት ለመግለፅ ሞክረናል፤ መተግበር ስላልቻሉ ሙሉ ለሙሉ ብልጫ ተወስዶብን ልንሸነፍ ችለናል።

ከባለፈው ጨዋታ አንፃር ስለወረደው ብቃታቸው…

ከመቻል ጋር ስንጫወት እንደዚህ ዓይነት የሜዳ ሁኔታ አልነበረም። ምክንያት ለመድርደር ሳይሆን ቅድም እንደገለፅኩልህ ነው። ሁልጊዜ በምትቀርብበት መንገድ ሳይሆን ሜዳው በሚፈቅደው መንገድ ነው መቅረብ ያለብህ ይሄንን ግን ተጫዋቾቼ አልተገበሩትም። አርባምንጭ ደግሞ የሜዳው ሁኔታ ተጠቅመው ጥሩ አካል ብቃትም ስላላቸው ብልጫ ወስደው ማሸነፍ ችለዋል።

\"\"