በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ሦስተኛ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በ 33 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ድሬዳዋ ከተማዎች በ 37 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ሲያገናኝ ለተመልካች ማራኪ የሆነ ፉክክር እንደሚደረግበት የሚጠበቀው ጨዋታ ቀን 9 ሰዓት ሲል ይጀመራል።
ከሽንፈት መልስ ወልቂጤ ከተማ ላይ ድል የተቀዳጁት ድሬዎች ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች ስድስት ነጥቦችን ቢያሳኩም አሁንም ከወራጅ ቀጠናው አራት ነጥቦችን ብቻ ርቀው ለመቀመጥ ሲገደዱ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ወልቂጤ ከተማን ሲረቱ በተለይም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ያደረጓቸው በትኩረት የተሞሉ እንቅስቃሴዎች ማሳካት ለሚፈልጉት ዕቅድ ትልቅ መነሳሻ ይሆናቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ብርቱካናማዎቹ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ያስቆጠሯቸው ሰባት ግቦች በተለያዩ ስድስት ተጫዋቾች መቆጠራቸው ደግሞ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪያቸውን ቢንያም ጌታቸውን ቢይዙም ቡድኑ በርካታ የግብ ምንጮች እንዳሉት የሚጠቁም ነው። ቡድኑ ውጤታማ ወደ ሚሆንበት የመስመር ተከላካዮች ያልተገደበ የማጥቃት እንቅስቃሴ መመለሱ እንደ ጠንካራ ጎኑ የሚጠቀስ ሲሆን ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለው እና የቀድሞ ክለቡን ይገጥም የነበረውን እንየው ካሳሁንን በጉዳት ማጣቱ ባለፈው ያገኘውን ጠንካራ ጎኑን እንዳያጣ ቢያሰጋውም አሰጋኸኝ ጴጥሮስም በቦታው ጠንካራ ተጫዋች እንደሚሆን ይጠበቃል።
ከአራት ጨዋታዎች በኋላ በሲዳማ ቡና ሽንፈት የገጠማቸው ፋሲሎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ቢወስዱም የግብ ዕድሎችን በመጠቀሙ በኩል የነበራቸው ደካማ እንቅስቃሴ ድል ላለማሳካታቸው ምክንያት ነበር። አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከጨዋታዉ በኋላ በሰጡት አስተያየት በተለይም ከፊት መስመር ላይ ያለው የተጫዋቾች ስብስብ ከመጀመሪያው ምልመላ ጀምሮ ስኬታማ እንዳልነበር በመጠቆም በዛ ምክንያትም ተከታታይ ድሎችን አለማሳካታቸውን መግለጻቸው ሲታወስ ቡድኑ ካለፉት 12 ጨዋታዎች 10 በሚሆኑት ግብ አስቆጥሮ መጠነኛ መሻሻል ላይ የነበረ ቢሆንም በቂ ባለመሆኑ ለተከታታይ ድሎች ከመቸገሩ በላይ በሊጉ አምስተኛውን ዝቅተኛ የግብ መጠን (26) ብቻ ማስቆጠራቸው ግን የአሰልጣኙን ሀሳብ የሚደግፉ ቁጥራዊ መረጃዎች ናቸው። ሆኖም ዐፄዎቹ በተከታታይ የሚገጥሟቸው ድሬዳዋ እና ወልቂጤ የመውረድ ስጋት ያለባቸው ቡድኖች በመሆናቸው ድል ለማሳካት ጠንካራ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
በድሬዳዋ በኩል ያሲን ጀማል ፣ ያሬድ ታደሰ ፣ ብሩክ ቃልቦሬ እና እንየው ካሳሁን በጉዳት ቢኒያም ጌታቸው እና ዮሴፍ ዮሐንስ ደግሞ በቅጣት ጨዋታው የሚያልፋቸው ሲሆን በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ በዛብህ መለዩ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ መሆኑ ሲረጋገጥ የፍቃዱ ዓለሙ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ 11 ጊዜያት ተገናኝተው ዕኩል አራት አራት ጊዜ ሲሸናነፉ በሦስቱ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹም ፋሲል 14 ድሬዳዋ ደግሞ 10 ግቦች አስቆጥረዋል።
ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ
ምሽት 12 ሰዓት ላይ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ እንደሚደረግ በሚጠበቀው መርሐግብር በአንድ ነጥብ ተበላልጠው 11ኛ እና 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ወሳኝ ሦስት ነጥብ ለማሳካት ብርቱ ፍልሚያ ያደርጉበታል ተብሎ ይገመታል።
ተከታታይ አራት ጊዜ የ 1-0 ድል ያሳኩት ሲዳማዎቸ በደጋፊዎቻቸው ታጅበው መጫወት ከጀመሩ በኋላ የሚቀመሱ አልሆኑም። በተለይም ከነዚህ አራት ጨዋታዎች በሦስቱ ጨዋታዎች ድል ያደረጉት በመጀመሪያው አጋማሽ መሆኑ እና ይልቁንም ሁለቱ ጨዋታዎች ላይ በመጀመሪያዎቹ 5 ደቂቃዎች ግብ አስቆጥረው መርታታቸው ቡድኑ በከፍተኛ የጨዋታ ስሜት በመጀመር የሚያደርገውን ጠንካራ እንቅስቃሴ ሲጠቁም በቀሪ ደቂቃዎች ግቡን አለማስደፈሩ ደግሞ ቡድኑ ቀውስ ውስጥ ለገባበት የውጤት ማጣት ምክንያት የነበረው የተከላካይ መስመሩ ወደ ትክክለኛ መስመር እየመጣ መሆኑን ያስመሰከረ ነው። ሲዳማዎች በሰሞንኛ ብቃታቸው ከነበሩበት የወራጅ ቀጠናው በመውጣት በወራጅ ቀጠናው ከሚገኘው ወልቂጤ ከተማ (29) እና አራተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ፋሲል ከነማ (37) ዕኩል የአራት ነጥቦች ልዩነትን ይዞ እንዲቀመጡ አስችሏቸዋል። ሆኖም በነገው ዕለት በአንድ ነጥብ ከሚበልጡት እና የመውረድ ስጋት ካለበት ሌላኛው ቡድን ወላይታ ድቻ የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል እንደማይሆን ይጠበቃል።
ለስምንት ያህል የጨዋታ ሳምንታት ድል ከናፈቃቸው በኋላ መቻል እና ለገጣፎ ላይ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ችለው የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች ግን በሁለቱ አቻ ሲወጡ በአንዱ ተሸንፈዋል። የተደላደለ ቦታ ላይ የተቀመጠ ይመስል የነበረው ቡድኑ ቀስ በቀስ በመንሸራተት ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥቦች ርቀት ላይ እንዲቀመጥ አድርጎታል። ከለገጣፎ ለገዳዲ (18) በመቀጠል ከሀዲያ ሆሳዕና ዕኩል ዝቅተኛውን የግብ መጠን(21) ያስቆጠሩት ድቻዎች ብዙ ከሚጠብቁበት ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪያቸው ቃልኪዳን ዘላለም ከሰባት ግቦች(33.33%) እና አንድ ለግብ አመቻችቶ ከማቀበል የበለጠ አስተዋጽኦ አለማግኘታቸው እንደ ምክንያት ይነሳ እንጂ የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ዐይናፋር የሆነው ስብስባቸው የግብ ዕድሎችን በመጠቀሙ በኩል ያለውን ደካማ አፈጻጸም በጊዜ ካልቀረፈ ችግር ውስጥ ሊከተው ይችላል። በአንድ ነጥብ ከፍ ብሎ ከተቀመጡት እና አራት ተከታታይ ጨዋታዎችን በማሸነፍ ወቅታዊ ድንቅ ብቃት ላይ ከሚገኙት ሲዳማዎች ጋር ለሚያደርጉት ፍልሚያም በሁሉም የሜዳ ክፍል ላይ የተለየ ጥንቃቄ የተሞላበት አቀራረብ ይዘው እንደሚገቡ ይጠበቃል።
በሲዳማ ቡና በኩል ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ያኩቡ መሐመድ በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች ያሬድ ዳዊትን በቀይ ካርድ ምክንያት አይጠቀሙም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 17 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ሁለት ጨዋታ ሲያሸንፍ በስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና ዘጠኝ ጊዜ አሸንፏል። በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 27 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 9 ፣ ሲዳማ ቡና 18 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።