ኢትዮጵያ ቡና በአማኑኤል ዮሐንስ እና መስፍን ታፈሰ ጎሎች ሀድያ ሆሳዕናን 2-1 በማሸነፍ ደረጃውን ከፍ አድርጓል።
ሀድያ ሆሳዕና የባህር ዳር ድሉ ላይ የተጠቀመበትን አሰላለፍ ሳይቀይር ለጨዋታው ሲቀርብ ከለገጣፎ ነጥብ የተጋሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንፃሩ ራምኬል ጀምስን በክዋኩ ዱሀ ፣ መሐመድ ኑርናስርን አብዱልከሪም ወርቁ ተክተው ቀርበዋል።
ቀዝቀዝ ባለ ዐየር ጅምሩን ያደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጎልን ያስመለከተን ገና 2ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። ከአማካይ ስፍራ ቦታው መስመር ወጥቶ ሲጫወት የነበረው እና በግራ የሜዳ ክፍል ለቡና የጥቃት መነሻ የሆነው ሮቤል ተክለሚካኤል ከተከላካይ ጀርባ የሀድያ ሆሳዕና ተጫዋቾች በተዘናጉበት ሰዓት ያሻገራትን ኳስ አማኑኤል ዮሐንስ ወደ ግብነት ቀይሯት ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ሀድያ ሆሳዕናዎች ራሳቸው ወደ ጨዋታ ለማስገባት በተቸገሩበት የመጀመሪያዎቹ ሀያ ያህል ደቂቃዎች ከቅጣት ምት ብሩክ ማርቆስ አክርሮ መትቶ በረከት አማረ በጥሩ ቅልጥፍና ያወጣበት እና ተመስገን ብርሀኑ በነበረበት ደካማ የውሳኔ አሰጣጥ ወደ ግብ ቢደርሱም ስሎች መሆን ግን አልቻሉም። ኳስን ከራስ ሜዳ በማስጀመር በይበልጥ የሮቤልን እንቅስቃሴ ለመጠቀም አልመው ከመነሻው ጀምሮ ይጫወቱ የነበሩት ቡናማዎቹ 19ኛው ደቂቃ ላይ ሌላ ጎል አግኝተዋል።
ሮቤል ለሁለተኛ ጊዜ በጥሩ ዕይታ ወደ ግብ የላካትን ኳስ መስፍን ታፈሰ በቄንጠኛ መልኩ ጎል አድርጓታል ለጎሉ መቆጠር የሴኔጋላዊው ግብ ጠባቂ ፔፕ ሰይዶ ሚና የጎላ ነበር።
ሁለት ያህል ግቦች ከተቆጠረባቸው በኋላ በሽግግር ለመጫወት ያለሙት ሀድያዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነት የሚገኙ ዕድሎችን መጠቀም አልቻሉም 28ኛው ደቂቃ ተመስገን የግል አቅሙን ተጠቅሞ ለፍቅረየሱስ ሰጥቶት በመጨረሻም ለብሩክ ሰጥቶት ተጫዋቹ አክርሮ መቶ በረከት አማረ አውጥቶበታል። ቡድኑ ተጨማሪ ዕድልን በዘካርያስ አግኝቶ በድጋሚ አምክነውታል። ጨዋታው 38ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የስታዲየሙ ፓውዛ እየበራ እየጠፋ በማስቸገሩ ጨዋታው አስር ደቂቃዎች ለመቋረጥ ተገዷል። ከተቋረጠበት ቀጥሎም ኢትዮጵያ ቡና መስፍን ታፈሰን በጉዳት በጫላ ተሺታ ካጣ በኋላ አጋማሹ በ2ለ0 ተገባዷል።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ሀድያ ሆሳዕናዎችን አንቅቶ በአንፃሩ ቡናን አቀዝቅዞ የቀጠለ ነበር። ሰመረ ሀፍታይን በባዬ ገዛኸኝ የተኩት ሀድያ ሆሳዕናዎች የማጥቂያ በራቸውን ተመስገን ብርሀኑ እና ባዬ ገዛኸኝን የትኩረት ማዕከል በማድረግ በድግግሞሽ ተጋጣሚያቸውን ማስጨነቅ ጀምረዋል። ኢትዮጵያ ቡናዎች አጋማሹ እንደተጀመረ ጫላ በግንባር ወደ ላይ የሰደዳት እና 55ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል መሬት ለመሬት የሰጠውን ኳስ ብሩክ በየነ ማስቆጠር የሚችለውን ፔፕን አሳቅፎታል። በመልሶ ማጥቃት ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ለመጫወት ያለሙት ሀድያዎች 57ኛው ደቂቃ ላይ ማራኪ ጎል አግተዋል። ተመስገን ብርሀኑ ወደ ቡና የግብ ክልል የግል ጥረቱን ተጠቅሞ እየገፋ ገብቶ ወደ ጎል ሲመታ በተከላካይ ተደርባ ስትመለስ በግምት ስትመለስ ከ30 ሜትር ርቀት ባዬ ገዛኸኝ አክርሮ መቶ በረከት አማረ መረብ ላይ አሳርፏታል።
በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበራቸው የጨዋታ ብልጫ እየወረዱ ለተጋጣሚያቸው ያስረከቡት ቡናማዎች ተከላካያቸው ኩዋኩ ዱሀ ራሱን የመሳት ጉዳት አስተናግዷል። ተጫዋቹ ሜዳ ላይ ህክምና ተደርጎለት የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ ማገገም አለመቻሉን ተከትሎ በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታል ለተጨማሪ ህክምና አምርቷል። በሌላ ክስተት ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና ምክትል አሰልጣኙ ነፃነት ክብሬ ከዳኛ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በቀጥታ ቀይ ከሜዳ ተወግዷል። በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች ሀድያ ሆሳዕና በቀጥታ እና በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት በተመስገን እና ባዬ አማካኝነት በተደጋጋሚ ወደ አቻነት ለመሸጋገር ጥረው በመጨረሻም የቡናን የመከላከል መንገድ መሻገር ከብዷቸው ጨዋታው በ2ለ1 የቡና ድል ተጠናቋል። ድሉም ቡናን በደረጃ ሰንጠዡ አራተኛ ላይ አስቀምጧል።