የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ጎፈሬ ስምምነት ፈፅመዋል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች በቀጣይ ጊዜያት የጎፈሬን ትጥቅ እንዲጠቀሙ የሚያደርገው ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈርሟል።

የኢትዮጵያ ዋናው የወንዶች ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም የሴቶች እና የዕድሜ እርከን ቡድኖች የሚጠቀሙበትን ትጥቅ የተመለከተ የፊርማ ሥነ ስርዓት ዛሬ ተከናውኗል። ከሰዓት በኋላ በቤስት ዋስተርን ፕላስ ሆቴል የተከናወነው ስምምነት በርካታ እንግዶች የታደሙበት ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና በትጥቅ አምራቹ ጎፈሬ መካከል የተደረገ ነበር።

\"\"

የስምምነቱን ዝርዝር ጉዳዮች ያካተተ ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሀፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ከቀድሞው ስፖንሰራቸው ኦምብሮ ጋር ስለነበራቸው የሥራ ግንኙነት በአጭሩ ካወሱ በኋላ ከውጪ ምንዛሪ እና እንደመንግሥት ከተቀመጡ አቅጣጫዎች መነሻነት እንዲሁም የሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲኖሩ ከሚያበረታታው የስፖርት ፖሊሲ አንፃር ወደ ሀገር ውስጥ አምራች መምጣታቸውን ተናግረዋል። በዚህም ቀደም ብሎ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ትጥቅ አቅራቢነት ባለፈ በኦምብሮ ያላሟላቸው ትጥቆችን በማሟላት የሥራ ግንኙነት ካለው ጎፈሬ ጋር ለቀጣይ አራት ወራት አብረው በአጋርነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ዋና ፀሀፊው ቀጥለውም በዚህ ጊዜ ውስጥ ዋናው ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከማላዊ እና ግብፅ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ እንዲሁም በክረምቱ በአሜሪካ ጉዞ የጎፈሬን ትጥቅ እንደሚጠቀም እና በተለያዩ የዕድሜ ዕርከን የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖችም ተጠቃሚ እንድሚሆኑ አስረድተዋል። አቶ ባህሩ እንዳሉት ጎፈሬ ከሌላው ዋጋው ሀምሳ በመቶው ቅናሽ በሆነ ዋጋ ትጥቆቹን እንደሚያቀርብም ተናግረዋል። የእስካሁኑ የሥራ እና የጥራት ዕድገታቸው በተለይም ከሀገር ውጪ እየሰሯቸው የሚገኟቸው ሥራዎች ለዛሬው ስምምነት እንዳደረሳቸው የተናገሩት የጎፈሬ ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን በበኩላቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ትጥቅ ማቅረባቸው በቀጣይ ሌሎች ዕድሎችንም እንደሚፈጥርላቸው ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

\"\"

በመቀጠል ሁለቱ ተቋማት አብረው ለመዝለቅ የተስማሙበትን ስምምነት በፊርማቸው አፅድቀው እና ጎፈሬ ለብሔራዊ ቡድኖቹ የሚያቀርባቸው ትጥቆች ለእይታ ከቀሩቡ በኋላ መርሐ ግብሩ ተፈፅሟል።