ሪፖርት | የአርባምንጭ ተጫዋቾች ያስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ከሲዳማ ጋር ነጥብ አጋርተዋል

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተደረገው የሲዳማ ቡና እና የአርባምንጭ ከተማ ጨዋታ 1ለ1 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ቡድኖቹ በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ባደረጉበት ለውጦቻቸው ሲዳማ ቡና ከድቻው የአቻ ውጤቱ አማኑኤል እንዳለን በደግፌ ዓለሙ እና እንዳለ ከበደን በይስሐቅ ከኖ ሲተኩ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ድልን ያሳኩት አርባምንጮች በበኩላቸው ወርቅይታደስ አበበን በአካሉ አትሞ እንዲሁም ቡጣቃ ሸመናን በአቡበከር ሻሚል ለውጠዋል።

\"\"

ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ጨዋታውን ሲዳማ ቡናዎች ማስጀመር ቢችሉም የጨዋታው የመጀመሪያ ሀያ ደቂቃዎችን ወደ መስመር በማድላት ይጫወቱ የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች አንፃራዊ ብልጫን ወስደው ተመልክተናል። በዚህም የጨዋታ መንገድ ገና 7ኛው ደቂቃ ላይ ጥራት ያላትን የግብ አጋጣሚ ፈጥረው ታይተዋል። ተመስገን እና እንዳለ ጥሩ አንድ ሁለት ንክኪን ከሜዳው የግራ አቅጣጫ አድርገው ተመስገን በጥሩ ዕይታ የሰጠውን አህመድ ሁሴን በግንባር ገጭቶ ፊሊፕ ኦቮኖ ቅልጥፍናውን ተጠቅሞ ከግብነት ታድጓታል። ሲዳማ ቡናዎች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች አጃህ እና ይገዙን የጥቃት መነሻ በማድረግ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም የሚጣሉ ኳሶቻቸው ለአርባምንጭ ተከላካዮች በቀላሉ ተገጭተው ይመለሱ ነበር። 9ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ከርቀት የመታት እና ከደቂቃዎች በኋላ ይገዙ የአሸናፊን መዘናጋት ተከትሎ ያደረጋት ያልተጠበቀች ሙከራ በቡድኑ በኩል የታዩ ተከታታይ አጋጣሚዎች ናቸው።


የሲዳማን የመከላከል ክፍተት ለመጠቀም የመስመር አጨዋወትን በይበልጥ የተጠቀሙት አርባምንጭ ከተማዎች መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። 18ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የደረሰችውን ኳስ እንዳልካቸው መስፍን ሳይቸገር መሐል ለመሐል የሰጠውን ኳስ ጊት ጋትኩትን አቅጣጫ አስቶ አህመድ ሁሴን መረቡ ላይ ኳሷን አሳርፏታል።

ጎል ካስተናገዱ በኋላ በጥልቀት አልፎ አልፎ ከርቀት በሚደረጉ እንዲሁም ከቆሙ ኳሶች አቻ ለመሆን የጣሩት ሲዳማ ቡናዎች በድግግሞሽ ጥቃትን ሰንዝረዋል። ደግፌ ዓለሙ ከርቀት ሞክሮ ይስሀቅ ተገኝ ካደነበት ሙከራ መልስ ሌላ አደገኛ ሙከራን አድርገዋል። 29ኛው ደቂቃ መሐሪ መና ከቅጣት አክርቶ መቶ ይስሀቅ ካወጣበት አደገኛ ሙከራ መልስ ሲዳማ ቡናዎች ጎል አግኝተዋል። አጋማሹ ሊገባደድ በተሰጠው ጭማሪ ሁለተኛ ደቂቃ ላይ አበባየው ዮሐንስ ከመሐል ሜዳ ከተጠጋ ቦታ የተገኘን ቅጣት ምት ወደ ጎል ሲያሻማ አህመድ እና አሸናፊ ለማውጣት ሲገባበዙ አሸናፊ ፊዳ ራሱ መረብ ላይ ደባልቋት ጨዋታው 1ለ1 ለዕረፍት አምርቷል።


ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ ከዕረፍት በፊት ጊት ጋትኩትን በጉዳት በያኩቡ የተኩት ሲዳማ ቡናዎች የነበረባቸውን የመሐል ሜዳ ክፍተት ለማስተካከል አቤል እንዳለን በሙሉቀን አዲሱ ለውጠው ቀርበዋል። በፉክክር ደረጃ የወረደ አቀራረብን ያስመለከተን አጋማሹ መሐል ሜዳ ላይ የሚደረጉ የኳስ ንክኪዎች የበዙበት ሲሆን በሙከራዎች ደረጃ ግን እምብዛም ነበር ፤ ሙከራን ለማየትም 80ኛው ደቂቃን መጠበቅ ግድ ብሏል።


በተጠቀሰው ደቂቃ ፊሊፕ አጃህ ላይ በአርባምንጭ በቀኝ የሜዳ ክፍል ወደ መስመር ከተጠጋ ቦታ የተሰራን ጥፋት ተከትሎ የተገኘችን ቅጣት ምት አበባየው ዮሐንስ ሲያሻማ አጃህ ጨረፍ አድርጓት በግቡ የላይኛው አግዳሚ የተመለሰችበት ተጠቃሿ ነች። አርባምንጮች በአንድ ለአንድ ግንኙነት አህመድ ተጠቅመው ለማስቆጠር ቢጥሩም ደካማ የነበረው የአጥቂ ክፍላቸው በቀላሉ ግብ እንዳያገኙ አድርጓቸዋል። ጨዋታውም ከነበረው የደበዘዘ መልክ አንፃር ተጨማሪ ግቦችን ሳያስመለክተን 1ለ1 ተቋጭቷል።

\"\"