መረጃዎች | 101ኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበናል።


ሀዋሳ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

ሁለት ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸው ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች አንዱ ነው ፤ ስለዚህ ጨዋታ ያዘጋጀናቸው አጫጭር መረጃዎችም እንደሚከትለው አዘጋጅተነዋል።

ወልቂጤ ከነማን ሦስት ለሁለት ካሸነፉ በኋላ በቀሩት አራት የሊግ ጨዋታዎች ሦስት ሽንፈት እና አንድ አቻ ያስመዘገቡት ሀዋሳዎች በነገው ጨዋታ ጨምሮ በቀሩት የሊግ ጨዋታዎች መሻሻል ካላሳዩ የወራጅነት ስጋት ስለሚያንዣብባቸው የነገው ጨዋታ ግድ የማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ብቻ የተቆጠሩበት ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ያለው የዘርዐይ ሙሉ ስብስብ ደካማ የፈጠራ ዐቅም ያለው አማካይ ክፍል መያዙ ቡድሉ ጥራት ያላቸው የጎል ዕድሎች እንዳይፈጥር እና ግቦች እንዳያስቆጥር ሳንካ ሆኖታል። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ጊዜያት የቡድኑ አንዱ ጠንካራ ጎን የነበረው የመስመር አጨዋወት መውረድም የራሱ ድርሻ አለው። በነገው ጨዋታም የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት መሻሻል በቡድኑ ውጤት ቀጥተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
\"\"
ለገጣፎ ለገዳዲና መቻልን በተከታታይ ካሸነፉ በኋላ በተከታታይ ሦስት አቻ እና አንድ ሽንፈት አስተናግደው ሦስት ነጥብ ማግኘት ያልቻሉት የጦና ንቦች እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ ላለመውረድ ከሚጫወቱ ቡድኖች በነጥብ ለመራቅ ይህንን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ሆነው ነው ወደሜዳ የሚገቡት። ጠጣር እና ለተጋጣሚ እምብዛም ክፍተት የማይሰጥ ወደ መከላከል ያዘነበለ አማካይ ክፍል ያላቸው አሰልጣኝ ፀጋዬ በነገው ጨዋታ የተሻለ የማጥቃት ዝንባሌ ያለው የአማካይ ጥምረት ይዘው ካልገቡ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር እንደሚቸገሩ እሙን ነው። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚነሳው ደግሞ የተጋጣሚያቸው ሀዋሳ ተከላካይ ክፍል ጠንካራነት ነው። ቡድኑ በነገው ጨዋታ ለማሸነፍም የግብ ዕድሎች ለመፍጠር እና ግቦች ለማስቆጠር ከወትሮው የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ያለው አጨዋወት ይዞ መግባት ይጠበቅበታል።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ዳንኤል ደርቤ ከወባ ህመሙ ቢያገግምም መሰለፉ አጠራጣሪ ነው። ከዛ በተጨማሪ ብርሀኑ አሻሞ በጉዳት፤ መሐመድ ሙንታሪ በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም። በወላይታ ድቻ በኩል ያሬድ ዳዊት ከቅጣት ተመልሷል። ይሁን እንጂ በሀይሉ ተሻገር እና አንተነህ ጉግሳ ከጉዳት አላገገሙም። በተጨማሪም ሳሙኤል ተስፋዬ ከክለቡ ጋር አይገኝም።

አዳማ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

በሁለት ተቃራኒ መንገድ ያሉት አዳማ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉት የነገው ሁለተኛ ጨዋታም እንደሚከተለው ዳሰነዋል።

ሲዳማ ቡናን ሦስት ግቦች አስቆጥረው ካሸነፉ በኋላ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት አቻና ሁለት ሽንፈት ያስተናገዱት አዳማዎች ደረጃቸውን ለማሻሻልና በሀዋሳ የመጀመርያ ድላቸው ለማግኘው አልመው ወደ ሜዳው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል። በውድድር ዓመቱ ግቦች ለማስቆጠር እና የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የማይቸገር ጥሩ የሚያጠቃ ቡድን ያስመለከቱን አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ቡድናቸው በወሳኙ ሰዓት የገጠመው የውጤት መንሸራተት የመቀልበስ ትልቅ ኃላፊነት ተሸክመው ወደ ነገው ጨዋታ ይገባሉ። ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች በአማካይ አንድ ግብ ብቻ ያስተናገደ የተከላካይ ክፍል ቢኖረውም በዚህ ሰዓት ዕድሎች ወደ ግብነት የሚቀይር ሁነኛ ተጫዋች በማጣቱ ጨዋታዎች ለማሸነፍ እንዲቸገር ሆኗል። በነገው ጨዋታም ይህንን ግብ የማስቆጠር ችግሩ መቅረፍ ቅድምያ የሚሰጠው ተግባር ነው።
\"\"
የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ በጥሩ የውጤት መነቃቃት የሚገኙት ብርቱካናማዎቹ በጥሩ ወቅታዊ አቋም ከሚገኙት ክለቦች ይጠቀሳሉ። ካለፉት አምስት ጨዋታዎች ያስመዘግቧቸው ሦስት ድሎች ለዚህ ትልቅ ማሳያ ናቸው። ከዚህ ቀደም ለስህተት ተጋላጭ የሆነ የተከላካይ ክፍል የነበራቸው ድሬዎች ምንም እንኳ በመድን ሦስት ግቦች ብያስተናግዱም ድክመታቸው በመጠኑም ቢሆን ደፍነዋል። በዚህ ወቅት ጥሩ የማሸነፍ ተነሳሽነት ያለው ቡድን የገነቡት አስራት አባተ በነገው ጨዋታ በተከታታይ ካሸነፈው ቡድናቸው ለውጥ ያደርጋሉ ተብሎ አይጠበቅም።

በአዳማ ከተማ በኩል አማኑኤል ጎበና በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም፤ የእዮብ ማቲዮስ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። ዳንኤል ደምሱም በቤተሰብ ችግር ምክንያት ቡድኑን የማያገለግል ሌላው ተጫዋች ነው። በድሬዳዋ ከኩልም ያሲን ጀማል፣ ያሬድ ታደሰ እና እንየው ካሳሁን በጉዳት ቡድናቸው የማያገለግሉ ተጫዋቾች ናቸው።