ሪፖርት | የባዬ ገዛኸኝ ሁለት ጎሎች ሀድያ ሆሳዕናን ባለ ድል አድርገዋል

ሀድያ ሆሳዕና ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2ለ1 በመርታት በደረጃ ሰንጠረዡ አራተኛ ላይ ተቀምጦ የሀዋሳ ቆይታውን አጠናቋል።

ሀድያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ ቡናው ሽንፈቱ በሦስት ተጫዋች ላይ ለውጥ አድርጎ ገብቷል። ፔፕ ሰይዶን በያሬድ በቀለ ፣ዳግም በቀለን በሔኖክ አርፊጮ ፣ ዘካሪያስ ፍቅሬን በባዬ ገዛኸኝ ሲተካ በአርባምንጭ ከተርታው ስብስባቸው ኤሌክትሪኮች ደግሞ ዮናስ ሰለሞንን በሚኪያስ መኮንን በብቸኝነት የተኩበት ለውጣቸው ሆኗል።

\"\"

ሳቢነቱ ወረድ ብሎ የታየው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የኋልዮሽ ቅብብሎች የተበራከቱበትን የጨዋታ መንገድ በመጀመሪያው አጋማሽ አስተውለናል። የጨዋታውን የመጀመሪያ ሀያ ያህል ደቂቃዎች ወደ መስመር በማድላት ለመጫወት የጣሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። 17ኛው ደቂቃ ላይ ለማጥቃት በቁጥር በዛ ብለው የተጓዙት ሀድያዎች በፈጠሩት ጫና የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ተከላካይ ማታይ ሉል ኳስን ለማራቅ ያደረገው ጥረት ደካማ መሆኑን ተከትሎ ባዬ ገዛኸኝ ነጥቆት ወደ ሳጥን ከገባ በኋላ ኳሷን ካክፓ መረብ ላይ አሳርፏታል።

እንቅስቃሴዎች ብቻ በበዙበት እንዲሁም ከሙከራዎች አንፃር ደካማ መልክ በነበረው ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ኳስን ሲያገኙ በፈጣን ሽግግር አብዱራህማንን ትኩረት አድርገው ይንቀሳቀሱ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ከጨዋታው መጀመር ጀምሮ ለስህተት ቅርብ የሆነው የሀድያን የመከላከል ድክመት ተጠቅመው አቻ ሆነዋል። 30ኛው ደቂቃ ላይ ጌቱ ሀይለማርያም ከቀኝ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ቃልአብ ውብሸት በግንባር ገጭቶ የያሬድ በቀለ ስህተት ታክሎበት ኳሷ ከመረብ አርፋ አቻ ሆነዋል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ሙሴ ካቤላ መሐል ለመሐል ያሾለከለትን ኳስ አብዱራህማን ሙባረክ ቢያገኛትም ሳይጠቀምባት ቀርቷል። በብዙ ነገሮች ደካማ የነበረው ጨዋታም 1ለ1 ተጋምሷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ በእንቅስቃሴም ሆነ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር በተሻለ ተነሳሽነት ሀድያ ሆሳዕናዎች ለመጫወት የሞከሩበትን አጨዋወት ያስተዋልን ቢሆንም የተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ግን የአጨራረስ ድክመት በግልፅ ይስተዋልባቸው ነበር። በአንፃሩ ወደ መስመር አድልቶ ለመጫወት በማሰብ አማካዩ ስንታየሁን በመስመር ተጫዋቹ ዮናስ በመተካት ወደ መስመር ያዘነበለ እንቅስቃሴ ያዘነበሉት ኤሌክትሪኮች እንደለውጡ የፈጠሩት ልዩነት እምብዛም ነበር። በተሻለ በድግግሞሽ የኤሌክትሪክ የግብ ክልል ይደርሱ የነበሩት ሀድያዎች ተመስገን ብርሀኑ ከቀኝ ወደ ጎል ሞክሮ ካክፖ በመለሰበት ዕድሎችን መሰንዘር ጀምረዋል።

የሰመረን ፣ የባዬ እና ፍቅረየሱስን ግልጋሎት በመጠቀም ከቆመ ኳስ ከርቀት እና በሚደረጉ ቅብብሎች ሙከራዎች በይበልጥ በመፍጠር ቀዳዳ ፍለጋ ላይ የተሰማሩት ሀድያዎች በሒደት ልዩነት እየፈጠሩ ሄደዋል። ከርቀት ባዬ ካደረጋት ሙከራ መልስ በተለይ ፍቅረየሱስ ከሳጥን ጠርዝ መቶ ካክፓ ከመለሳት እና በድጋሚ ባዬ እና ተቀይሮ የገባው ፀጋዬ ብርሀኑ ጥራት ያላቸውን ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው ከመለሰባቸው በኋላ ባሉት ቀሪዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ እየነቁ የሄደው ጎል አስቆጥረዋል። 75ኛው ደቂቃ ላይ ሰመረ ከቀኝ ወደ ውስጥ የግል ጥረቱን አክሎ የሰጠውን ፍቅረየሱስ በጥሩ ዕይታ አብርዶለት ባዬ ገዛኸኝ ለራሱም ሆነ ለክለቡ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል። ከደቂቃዎች መልስ ሰመረ ሀፍታይ ግብ አስቆጥሮ የነበረ ቢሆንም ግቧ ከጨዋታ ውጪ ተብላለች። ሀድያዎች እንደነበራቸው ብልጫ በመጨረሻም 2ለ1 አሸናፊ ሆነው ደረጃቸውን ወደ አራት አሳድገዋል።

\"\"