ጠንካራ ፉክክርን ያስመለከተን የባህርዳር ከተማ እና መቻል ጨዋታ በመጨረሻም በባህርዳር ከተማ 3ለ2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
መቻሎች በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ከሀዋሳ ጋር ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በሁለቱ ላይ ለውጥ አድርገዋል። ሳሙኤል ሳሊሶ እና ግርማ ዲሳሳን በበረከት ደስታ እና ከነዐን ማርክነህ ሲተኳቸው በ25ኛው ሳምንት ጨዋታ ባህርዳሮች በሀድያ ሆሳዕና ሽንፈት ከገጠመው ስብስባቸው አደም አባስን በፍፁም ጥላሁን ብቸኛ ቅያሪያቸው ሆኗል።
የጨዋታው የመጀመሪያ አስራ አምስት ደቂቃዎች ደከም ብሎ የሚታይ እንቅስቃሴዎችን ያስመለከተን ቢሆንም መሐል ሜዳውን በአግባቡ በመቆጣጠር በመስመር በኩል የፈጣን ተጫዋቾችን ዕገዛ ተጠቅመው ቀስ በቀስ መጫወት የጀመሩት ባህርዳሮች ጨዋታውን ወደ ራሳቸው ቁጥጥር ስር አድርገው በተደጋጋሚ በተጋጣሚያቸው ላይ ጥቃትን ሰንዝረዋል። ኳስን ከራስ ሜዳ በሚደረጉ ቅብብሎች ኋላ ላይም ወደ እስራኤል እና በረከት ባመዘነ መልኩ ይጣሉ በነበሩ ኳሶች የጥቃት መነሻቸው ሆኖ መቻሎች ቢንቀሳቀሱም ፍሬያማ ሊያደርጋቸው አልቻለም ፤ ተሾመ በላቸው ከርቀት ሞክሮ በላይኛው ብረት የወጣችበት የቡድኑ ቀዳሚ ጥቃትም ጥራቷን ያልጠበቀች ሙከራቸው ሆናለች።
በአንፃሩ ሲያጠቁ ጥሩ የነበሩት ባህርዳሮች 19ኛው ደቂቃ ላይ ፍራኦል ከግራ ያሻማውን አብስራ መቶ ውብሸት ጭላሎ ከያዘበት ከሁለት ደቂቃዎች መልስ ጎል አግኝተዋል። በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል የመቻል ሳጥን ውስጥ ደርሰው የአብስራ እና ፍፁም በመጨረሻም ፍፁም ያቀበለውን ሀብታሙ ታደሠ ጎል አድርጓታል። ጎሏ ስትቆጠር ተከላካዩ ቶማስ ስምረቱ ጫማ ለመለወጥ ውጪ በመሆኑ ዳኛው ቶሎ እንዲገባ አላደረጉም በሚል መቻሎች ቅሬታን ሲያሰሙ ታዝበናል። ሦስቱን የፊት ተሰላፊዎች ፍፁም ፣ ሀብታሙን እና ዱሬሳን በመጠቀም የመቻልን የተከላካይ ክፍል ሲረብሹ የታዩት ባህርዳሮች 26ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ልዩ የነበሩት ዱሬሳ እና ፍፁም ተቀባብለው ፍፁም የመጨረሻውን ኳስ ሲሰጠው ሀብታሙ ታደሠ ሁለተኛ ጎል አድርጎታል።
ከቆመ ኳስ በፍራኦል ሞክረው ውብሸት ከያዘባቸው እና ፍራኦል ከመስመር አሻምቶ ዱሬሳ በግንባር ገጭቶ ከተያዘበት ሙከራ መልስ ሦስተኛ ግባቸውን ወደ ካዝናቸው ከተዋል። 40ኛው ደቂቃ ላይ ዱሬሳ ወደ ውስጥ እየነዳ ገብቶ ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ፍፁም ሲሰጠው ተጫዋቹ ወደ ጎል ሲመታው ምንተስኖት አዳነ ለማውጣት ሲዳዳ መረብ ላይ ኳሷን አሳርፏታል። ሦስት ጎሎችን ለማስተናገድ ከተገደዱ በኋላ ወደ ጨዋታ ለመሳብ ጥቂት ሙከራን ያደረጉት መቻሎች በረከት እና ተሾመ አከታትለው ሙከራ አድርገው ነበር። በተለይ በረከት መቶ የግቡ አግዳሚ ከመለሠችበት በኋላ አጋማሹ በ3ለ0 የባህርዳር ውጤት ተገባዷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ መቻሎች የሦስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገው ተመልሰዋል። እስራኤል እሸቱ ፣ ተሾመ በላቸው እና አህመድን ረሺድን በምንይሉ ወንድሙ ፣ ዮሐንስ መንግስቱ እና ግርማ ዲሳሳ ለውጠዋል። ከመጀመሪያው አጋማሽ በእጅጉ ተሻሽለው የተገኙት መቻሎች የከነዐን ምንይሉን እና በረከትን ጥምረት መጠቀም እንደ ጀመሩ ወደ ጨዋታ የምትመልሳቸውን ጎል አግኝተዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ከነዐን ማርክነህ ከተከላካዮች መሐል ያሳለፈለትን ኳስ በረከት ደስታ ከመረብ አዋህዷታል። ጥንቃቄ አዘል ጨዋታን በመምረጣቸው ራሳቸውን ጫና ውስጥ የከተቱትን ባህርዳሮች በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ኳስን ሲያገኙ ለመጫወት ቢጥሩም ከቀዳሚው አርባ አምስት መቀዛቀዞች ታይቶባቸዋል።
መቻሎች መሐል ሜዳውን ተቆጣጥረው በተሻለ ፍላጎት ወደ ቅኝት በይበልጥ ቢሳቡም ጥቃት ሲሰነዝሩ የወጥነት ክፍተት በሚገባ ይታይባቸው ስለ ነበር ተጨማሪ ጎል ማግኘት አላስቻላቸውም። በአንፃሩ ጥንቃቄ አዘል ነገር ግን በፈጣን መልሶ ማጥቃት ፍፁም ይጠቀሙ የነበሩት ባህርዳሮች ሌላ ዕድል አግኝተው ነበር። አለልኝ አዘነ ከውብሸት ጭላሎ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግብ ጠባቂው ካዳነበት ሙከራ መልስ መቻሎች ሁለተኛ ጎል አግኝተዋል። ምንይሉ ወንድሙ በረከት ጥጋቡ የሰራውን ስህተት ተከትሎ ግልፅ አጋጣሚን ካመከነ ከአንድ ደቂቃ መልስ ከማዕዘን ከተሻማ ኳስ በግንባር አስቆጥሮታል። የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ጫናዎችን የፈጠሩት መቻሎች በግሩም የርቀት አደገኛ ሙከራን አድርገው የነበረ ቢሆንም ጨዋታው በባህርዳር የ3ለ2 ድል ተጠናቋል።