ድሬዳዋ ከተማ የዲሲፕሊን ውሳኔ ተላልፎበታል

ድሬዳዋ ከተማ በተጫዋቹ በቀረበበት አቤቱታ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ አስተላልፏል።
\"\"
በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ የዘንድሮ ውድድር ዓመት ከመጀመሩ በፊት ከአራት ተጫዋቾቹ ጋር ለመለያየት ድርድር ተቀምጦ እንደነበር ይታወሳል። ከአራቱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ የሆነው አማካዩ ዳንኤል ኃይሉ በድርድሩ ሳይስማማ ቀርቶ ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ዲሲፕሊን ኮሚቴ እንደወሰደው አይዘነጋም። ተጫዋቹም ከነሀሴ ወር ጀምሮ ደሞዝ አልተሰጠኝም በማለት የጠየቀውን ጥያቄ ሲመለከት የነበረው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን ኮሚቴ የተጫዋቹን ጥያቄ በመንተራስ ክለቡን ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቆ ነበር። ክለቡ በምስክሮች በሰጠው ምላሽ ተጫዋቹ ያለፍቃድ የዝግጅት ጊዜውን አቋርጦ እንደወጣና ውል ለማቋረጥ የቀረበውን ድርድር አለመቀጠሉን ጠቅሷል።
\"\"
የአቤቱታ አቅራቢውን ጥያቄ እና የተጠሪውን ምላሽ ያዳመጠው የዲሲፕሊን ኮሚቴም በመመሪያ አንቀፅ 89 (ሀ) መሠረት የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቷል። በዚህም ክለቡ ለተጫዋቹ ከነሐሴ 2014 ጀምሮ እስከ ውል ማብቂያው ድረስ ያልከፈለውን ደሞዝ በ7 ቀናት ውስጥ እንዲከፍል አለበለዚያ ከተቀመጠው ቀነ ገደብ ውጪ የዘገየበት በየቀኑ ሁለት ከመቶ መቀጮ ጨምሮ እንዲከፍል አዟል። ክለቡ ይግባኝ የማለት መብት ቢሰጠውም ቅጣቱን ካልፈፀመ ከዝውውር እንዲታገድና ከፌዴሬሽኑ ምንም አይነት አገልግሎት እንዳያገኝ ተወስኗል።