“ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ትልቅ ገፅታ የሚፈጠር ደጋፊም ያለው ክለብ ነው” አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ

ሻሸመኔ ከተማን ከ15 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳደጉት አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ አጠር ያለ ቆይታን ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አድርገዋል።

\"\"

የ2015 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር በሦስት ምድቦች ተከፍሎ የአንደኛውን ዙር ጨምሮ በስድስት የተለያዩ ከተሞች ተደርጎ ተጠናቋል። በውድድሩ ምድብ ለ አራት ጨዋታዎች እየቀሩት ከ15 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ሻሸመኔ ከተማ በቀድሞው የመድን ተጫዋች እና አሰልጣኝ እንዲሁም አቃቂ ቃሊቲንም የማሰልጠን ዕድል በነበራቸው አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ (አግሮ) እየተመራ ነበር ማደግ የቻለው ውድድሩን በየስፍራው እየገኘች ስትዘግብ የነበረችው ሶከር ኢትዮጵያም ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ጋር ስለ ውድድር ዓመቱ ጉዞ አጠር ያለ ቆይታን አድርጋለች።

የውድድር ዓመቱ ጉዞ ምን ይመስላል ከሚለው እንጀምር ?

\”እንደሚታወቀው የከፍተኛ ሊግ ውድድር የግድ አንደኛ መውጣት ነው ያለብህ ስለዚህ ከመጀመሪያው ከተጫዋቾች ስብሰባ ጀምሮ ከተማዋን ሊመጥኑ የሚችሉ ተጫዋቾችን በማሰባሰብ ነው የጀመርነው። በአንደኛው ዙር ጥሩ ውጤት ነበረን እንደታየውም ቡድናችን አስቀድሞ ያረጋገጠበት ሁኔታ ነው ያለው።\”

በመጀመሪያው ዙር በአዲስ አበባ ተበልጣችሁ ነበር ዙሩን ያጠናቀቃችሁት በሁለተኛው ዙር ግን በምን ዓይነት መልኩ ተሻሽላችሁ ነው ለዚህ የበቃችሁት ?

\"\"

\”በጎደለን ቦታ ላይ ለምሳሌ የአጥቂ ክፍላችን ትንሽ ደካማ ሆኖ ይታይ ነበር አንደኛው ዙር ላይ በሁለተኛው ዙር እዛ ላይ መሻሻል አሳይተን ቶሎ ደሞ ከሜዳችን ወጥተን በማጥቃት ሂደት ውስጥ ኳሱን አፍጥነን ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል እንድንሄድ በማድረጋችን ይህን ውጤት አግኝተናል።\”

ሻሸመኔ ከ15 ዓመታት በኋላ ነው ያደገው እና እንደ አሰልጣኝ ቡድኑን በመመለስህ ምን ተሰማህ ?

\”እኔ ስመጣ እንደዚህ አልጠበኩም ፣ እንደዚህ እግርኳስ የሚወድ ማኅበረሰብ መኖሩንም አላውቅም ነበር እና በጣም ትልቅ ተነሳሽነት ነው ያየሁት። ትልቅ ከተማ ነው ፤ ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ትልቅ ገፅታ የሚፈጠር ደጋፊም ያለው ክለብ ነው እንግዲህ አንድ ክስተት ይሆናል ብዬ ነው የማስበው።\”

የስኬታችሁ ሚስጥር ምንድነው ?

\”የስኬታችን ምስጥር ትጋት ነው። እያንዳንዱ ሥነምግባር ላይ ሥርዓት ይዘን ተጫዋቾቼ ያንን ነገር እንዲተገብሩት ማድረጋችን ነው የስኬታችን ሚስጥር እሱ ነው። ስለዚህ ያንን እንዲያከናውኑ የተሰጣቸውን ታክቲካል ዲሲፕሊን እየተገበሩ ፤ ከዛ በተረፈ የዲሲፕሊን መንፈሳቸውን ጠብቀው በመጓዛቸው የመጣ ነው ስኬቱ።\”

ብዙ ጊዜ የሚያድጉ ክለቦች በገቡበት ዓመት የመውረድ አደጋ ውስጥ ይገባሉ እና ይሄንን እንዴት ለመወጣት አስባችኋል ?

\”እኛ ያው ካለፉት የምንማራቸው ነገሮች አሉ። እኔ እርግጠኛ ነኝ በወጣቶች የተሞላ ክስተት የሆነ ቡድን ይዘን እንቀርባለን ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም ተጫዋቾቹ ወደ ምልመላ ሲገቡ ራሱ በጣም በችኮላ ነው የሚያደርጉት እና ከእነርሱ ተምረን አሁን በጊዜ የምልመላ ሂደታችንን አድርገን በወጣት የተሞላ ቡድን ይዘን ለመቅረብ እንሞክራለን።\”

አቃቂን ከዚህ በፊት ወደ ከፍተኛ ሊግ አሳድገሃል መድንን አሰልጥነሃል በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ተጫውተሃል። በአሰልጣኝነት ካሁን በኋላ በምን ደረጃ እንጠብቅህ ?

\”እንደውም ዘግይቻለሁ። ጥሩ ውጤቶችን አስመዝግቤያለሁ እንዳልከው አቃቂ እና መድን ላይ አሁን ደግሞ ፕሪምየር ሊግ ገብቼ ክስተት የሆነ ቡድን ሠርቼ እርግጠኛ ነኝ ጥሩ ውጤት የማመጣ ይመስለኛል።\”

በመጨረሻ የምታመሰግናቸው ካሉ ?

\”ሁሉም የሻሸመኔ ደጋፊዎች ፣ አመራሮች ይህንን ክለብ ሲደግፉ ለነበሩ በሙሉ ፣ ተጫዋቾቼን እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን በሙሉ አመሠግናለሁ\”።

\"\"