መረጃዎች | የጨዋታ ቀን 104

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 28ኛ ሳምንት የመጀመርያ ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

ላለመውረድ በመታገል ላይ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ እና መውረዱን ያረጋገጠው ለገጣፎ ለገዳዲ የሚያገናኘው የሳምንቱን የመጀመርያ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

በተከታታይ አራት ጨዋታዎች አቻ ከወጡ በኋላ አሰልጣኛቸው አሰናብተው ኢትዮ ኤሌክትሪክን አራት ለባዶ በሆነ ውጤት ያሸነፉት አዞዎቹ በአዲሱ አሰልጣኝ ከሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ ሰብስበው ላለመውረድ በመታገል ላይ ይገኛሉ።
ሠላሳ ነጥቦች በመሰብሰብ ከላይ ካሉት ቡድኖች በቅርብ ርቀት የሚገኙት አርባ ምንጮች በሊጉ ለመቆየት ከተከታታይ አቻ ውጤቶች ተላቀው ከለገጣፎ ለገዳዲ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ጋር ካለባቸው የሊጉ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች በቂ ነጥብ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል። በግቦች ከተንበሸበሹበት የኤሌክትሪኩ ጨዋታ ውጪ በነበሩት የመጨረሻ አራት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠሩት እና የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገሩ የሚስተዋሉት አዞዎቹ በነገው ጨዋታ ጨምሮ በቀሩት ሦስት የሊጉ ጨዋታዎች ይህንን ችግር መቅረፍ ግድ ይላቸዋል።

\"\"

ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት ከአዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ሰብስበው በሊጉ መሪ ሽንፈት የገጠማቸው መውረዳቸው ያረጋገጡት ለገጣፎዎች ባለፉት ሳምንታት ጠንካራ ቡድኖች ገጥመው በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ አሳይተዋል። ቡድኑ ቀድሞ ከመውረዱ አንፃር በእንቅስቃሴ እና በሥነ-ልቦና ይወርዳል ተብሎ ቢጠበቅም በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ያሳየው ተጋድሎ ግን በቀጣይ ጨዋታዎች ቀላል ተጋጣሚ እንደማይሆን ማሳያ ነው።

በአርባምንጭ ከተማ በኩል ወርቅይታደስ አበበ ከጉዳት ሲመለስ አሸናፊ ፊዳ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆኗል። በለገጣፎ ለገዳዲ በኩልም የታምራት አየለ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው ሲሆን አንድ ጨዋታ የተጫወተው ሱሌይማን ትራኦሬ እና አማኑኤል አረቦም በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።

ወላይታ ድቻ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ሁለት በተቀራራቢ ነጥብ ላይ የሚገኙ ክለቦች የሚያገናኘው እና ምናልባትም የደረጃ ለውጥ ሊያስከትል የሚችለው ተጠባቂ ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ለገጣፎን ካሸነፉ በኋላ በተቀሩት አምስት የመጨረሻ ጨዋታዎች ድል የራቃቸው የጦና ንቦች በተጠቀሱት ጨዋታዎች ስድስት ግቦች አስተናግደው ሥስት ግቦች ብቻ አስቆጥረዋል። ይህ ማለት በአማካይ በአንድ ጨዋታ 0.5 ግቦች አስቆጥረዋል ማለት ነው። ቁጥሩ እንደሚያመላክተንም ቡድኑ ባለፉት ጨዋታዎች ደካማ የማጥቃት ስኬት እንደነበረው ነው። ቡድኑ በነገው ጨዋታ ጨምሮ በተቀሩት የሊጉ ጨዋታዎችም ይህንን ደካማ የማጥቃት ክፍሉ ማሻሻል ተቀዳሚ ሥራው ማድረግ ይጠበቅበታል። ይህንን ጨዋታ የተከላካይ ክፍሉን ካሻሻለው ድሬዳዋ ከተማ መሆኑም ፈታኝ ያደርገዋል። ሊጉ ከተጀመረ ጀምሮ ከቅዱስ ግዮርጊስ እና ከሀዋሳ ከተማ ጋር ካደረጋቸው እና ሦስት ለባዶና ሦስት ለአንድ ከተጠናቀቁ ጨዋታዎች ውጪ ከአንድ የግብ ልዩነት በላይ ገብቶበት ያልተሸነፈው ይህ ቡድን ተከላካይ ክፍሉ እና ጠጣር አማካዩ ጠንካራ ጎኖቹ ናቸው።

የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረጉ በኋላ መሻሻሎች አሳይተው ደረጃቸው ያሻሻሉት ብርቱካናማዎቹ በሀዋሳ ስኬታማ ጊዜ አሳልፈዋል። ቡድኑ በሀዋሳ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሦስት አሸንፎ በሁለት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል። በተጠቀሱት ጨዋታዎችም ሰባት ግቦች (1.7 ግቦች በጨዋታ) አስቆጥሮ በተመሳሳይ ሰባት ግቦች ተቆጥሮበታል። ሠላሳ ስድስት ነጥቦች ሰብስቦ በአስራ አንደኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ጥሩ መሻሻሎች ብያሳይም አሁንም ከወራጅነት ስጋት አልተላቀቀም። የነገው ተጋጣሚውም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ስለሚገኝ ከባድ ፈተና እንደሚገጥመው ለመገመት አያዳግትም። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በአማካይ 1.4 ግቦች በጨዋታ ያስቆጠረው የቡድኑ አጥቂ ክፍል የነገው ተጋጣሚው ወላይታ ድቻ የተከላካይ ክፍል ጠንካራነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ይታመናል።

\"\"

በድሬዳዋ ከተማ በኩል ያሲን ጀማል እና ያሬድ ታደሰ በጉዳት አይሰለፉም። በወላይታ ድቻዎችም ሳሙኤል ተስፋዬ ፣ በኃይሉ ተሻገር ፣ በረከት ወልደዮሐንስ እና አንተነህ ጉግሳን በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አይጠቀሙም።