ሪፖርት | አዞዎቹ ወሳኝ ድል በማግኘት ከወራጅ ቀጠናው ወተዋል

አርባምንጭ ከተማ ለገጣፎ ለገዳዲን በማሸነፍ በርካታ ሳምንታት ከነበረበት የወራጅ ቀጠና ወጥቷል።

በ27ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከሲዳማ ቡና ጋር አንድ ነጥብ የተጋሩት አርባምንጭ ከተማዎች ሦስት ተጫዋቾችን ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል። በለውጦቹም አካሉ አትሞ፣ አሸናፊ ፊዳ እና አቡበከር ሻሚልን በወርቅይታደስ አበበ፣ አበበ ጥላሁን እና ቡጣቃ ሸመና ተክተዋል። በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጫውተው የተረቱት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በበኩላቸው ኤሊያስ አታሮ፣ ተስፋዬ ነጋሽ፣ አማኑኤል አረቦ እና መሀመድ አበራን አሳርፈው አስናቀ ተስፋዬ፣ አቤል አየለ፣ ሱራፌል ዐወል እና ካርሎስ ዳምጠውን አሰላለፍ ውስጥ አስገብተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

ላለመውረድ ነጥቦችን እጅግ አጥብቀው የሚሹት አርባምንጭ ከተማዎች በ5ኛው ደቂቃ የጨዋታውን የመጀመሪያ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ በቀኝ መስመር ተከላካያቸው ወርቅይታደስ አበበ አማካኝነት ሰንዝረው ተመልሰዋል። በተቃራኒው ለገጣፎ ለገዳዲዎች በበኩላቸው በ14ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር የተሻማን ኳስ ኢብሳ በፍቃዱ በግንባሩ ወደ ግብ ሞክሮት በራሳቸው በኩል ቀዳሚውን ሙከራ አድርገዋል።

በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በተደጋጋሚ የመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ ላይ በመገኘት በአንፃራዊነት የተሻሉት አርባምንጭ ከተማዎች በዋናነት አህመድ ሁሴንን ማዕከል ያደረጉ ኳሶች እየላኩ ግብ ፍለጋ ይዘዋል። በ22ኛው ደቂቃም የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም አስናቀ አሸናፊ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አህመድ ሁሴን ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ከግቡ በኋላ ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር ያስመለከተን ጨዋታው ቀጣዩን ሙከራ በ35ኛው ደቂቃ አስተናግዶ ተጨማሪ ግብ አግኝቷል። በተጠቀሰው ደቂቃም መላኩ ካርሎስ ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል ዐወል በድንቅ ሁኔታ በቀጥታ በግራ እግሩ በመምታት ግብ አድርጎት ለገጣፎን ወደ ጨዋታው መልሷል። ጣፎ የአቻነቱን ግብ ካገኘ ከደቂቃ በኋላ ግን ቀሪ ደቂቃዎችን የሚያከብድበት ሁነት ተከስቷል። በዚህም የፍፁም ቅጣት ምቱ ሲሰጥ ጥፋት የሰራው አስናቀ ሌላ ጥፋት ወርቅይታደስ ላይ ሰርቶ በሁለት ቢጫ ከሜዳው ተሰናብቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾችን በመቀየር የሜዳ ላይ አጥቂዎቻቸውን ቁጥር አራት ያደረሱት አርባምንጮች ዳግም ወደ መሪነት ለመሸጋገር ማጥቃት ላይ ትኩረት ያደረገ አጨዋወት ሲከተሉ ተስተውሏል። በተለይ በ54ኛው ደቂቃ የጣፎው የግብ ዘብ ኮፊ ሜንሳ የሰራውን ስህተት ተከትሎ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የተሰጠውን ሁለተኛ የቅጣት ምት በመጠቀም ያደረጉትን የግብ ማግባት አጋጣሚ ለግብ የቀረቡበት ነበር።

ጨዋታውን በጥሩ ሁኔታ እየተቆጣጠሩ የሚገኙት አርባምንጮች በ61ኛው ደቂቃ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል። በዚህም አህመድ ሁሴን ከቀኝ መስመር ወርቅይታደስ ያሻማለትን ኳስ ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል። መከላከሉ ላይ ትኩረት አድርገው ሲጫወቱ የታዩት ለገጣፎዎች መልሶ ማጥቃቶችን በመጠቀም አደጋ ለመፍጠር ቢወጥኑም ሀሳባቸው በሚገባ መስራት አልቻለም። ይባስ በ67ኛው ደቂቃ ሦስተኛ ግብ በእንዳልካቸው እና ተመስገን ድብቅ ቅብብል በተገኘ አጋጣሚ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ነበር። በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎችም ሌሎች አራት ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል ተፈጥሮባቸዋል። በርካታ ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች የተጫወቱት ጣፎዎች በክፍት ጨዋታ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታውን ተሸንፈው ወተዋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ የለገጣፎ ለገዳዲው አሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ከሊጉ ቀድመው ቢወርዱም ለውድድሩ ድምቀት በጨዋነት መጫወት እንደሚፈልጉ ገልፀው በጨዋታው የተቻላቸውን ማድረጋቸውን አስረድተው የተሰጠባቸው የፍፁም ቅጣት ምት ባያሳምናቸውም ተጋጣሚያቸውን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ድል ያደረጉት አርባምንጭ ከተማ አሠልጣኝ በረከት ደሙ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበር አመላክተው የነበሩበት ደረጃ የራስ መተማመናቸውን ቢሸረሽርም ሶስት ነጥብ የግድ ለማግኘት ተጭነው ቢጫወቱም ለድል የነበረ ችኮላ ትንሽ ቅርፃቸውን ቢቀይርም በድሉ ደስተኛ እንደሆነ ገልፀዋል።ከጨዋታው በኋላ የለገጣፎ ለገዳዲው አሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ከሊጉ ቀድመው ቢወርዱም ለውድድሩ ድምቀት በጨዋነት መጫወት እንደሚፈልጉ ገልፀው በጨዋታው የተቻላቸውን ማድረጋቸውን አስረድተው የተሰጠባቸው የፍፁም ቅጣት ምት ባያሳምናቸውም ተጋጣሚያቸውን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ድል ያደረጉት አርባምንጭ ከተማ አሠልጣኝ በረከት ደሙ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበር አመላክተው የነበሩበት ደረጃ የራስ መተማመናቸውን ቢሸረሽርም ሶስት ነጥብ የግድ ለማግኘት ተጭነው ተጫውተው የነበረ ቢሆንም ለድል የነበረ ችኮላ ትንሽ ቅርፃቸውን እንደረበሸባቸው ጠቁመው በድሉ ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀዋል።