መረጃዎች | 105ኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 28ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

አዳማ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

ቀን 9 ሰዓት ላይ 36 ነጥቦችን በመያዝ 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን አዳማዎች በ 39 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ሀዲያዎች ጋር ሲያገናኝ ሁለቱም ቡድኖች ባለፈው ሳምንት ያገኙትን ድል በድጋሚ ለማሳካት ጥሩ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአምስት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ድሬዳዋ ከተማን ከመመራት ተነስተው በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2-1 በመርታት ወደ ድል የተመለሱት አዳማዎች ከድሉ ባሻገርም ሳምንቱ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ያስቆጠሩበት ነበር። ውድድሩ በድጋሚ ወደ መቀመጫ ከተማቸው መመለሱ በደጋፊዎቻቸው ታጅበው እንዲጫወቱ በማድረጉ በኩል የሚኖረው ሚና ትልቅ ሲሆን የነገው ተጋጣሚያቸው ሀዲያ ሆሳዕና ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ (17) በመቀጠል ሁለተኛውን ዝቅተኛ የግብ መጠን (19) ያስተናገደ ጠንካራ የተከላካይ መስመር መያዙ በአራት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ላስቆጠረው የአጥቂ መስመራቸው ፈተና ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"

ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ባህርዳር ከተማን በመርታት ወደ ድል የተመለሱት ሀዲያዎች በቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ቢያጋጥማቸውም መውረዱን ያረጋገጠውን ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2-1 በመርታት ወደ ድል ተመልሰዋል። የጠንካራ የተከላካይ መስመር ባለቤት ለሆኑት ነብሮቹ ደካማ የነበረው የአጥቂ መስመራቸው ባለፉት 3 ጨዋታዎች ላይ 5 ግቦችን ማስቆጠሩ የሚፈልጉት መሻሻል ነው። በደረጃ ሠንጠረዡ 4ኛ ደረጃ ላይ ይቀመጡ እንጂ ከቡድኖቹ የውጤት መቀራረብ አንጻር ከወራጅ ቀጠናው በስድስት ነጥቦች ብቻ ርቀው መቀመጣቸው ምንም የሚያሰጋቸው ባይሆንም በቀጣይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ መድን ጋር የሚገናኙ በመሆኑ የተደላደለ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ድሉን ይፈልጉታል።

በአዳማ ከተማ በኩል የዊልያም ሰለሞን እና አብዲሳ ጀማል ከቡድኑ ጋር አለመኖር በተጨማሪ አድናን ረሻድ እና አቡበከር ወንድሙ በቅጣት የነገው ጨዋታ የሚያልፋቸው ሲሆን በሀዲያ በኩል ደግሞ ፍሬዘር ካሳ ከቅጣት ተመልሷል። በአንጻሩ ቤዛ መድህን በጉዳት የማይኖር ሲሆን የብርሀኑ በቀለ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 7 ጊዜ ተገናኝተው አዳማ ከተማ 3 ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ 2 ጊዜ ሲያሸነፉ ሁለቱ ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። አዳማ 7 ሀዲያ ደግሞ 6 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ሀዋሳ ከተማ

12 ነጥቦችን ብቻ በመሰብሰብ ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 38 ነጥቦችን በመያዝ 7ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ ሲያገናኝ በኤሌክትሪኮች በኩል ለክብር በሀዋሳዎች በኩል ደግሞ ደረጃ ለማሻሻል የሚያደርጉት ፍልሚያ ምሽት 12 ሰዓት ላይ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

በውድድር ዓመቱ ሦስት አሰልጣኞችን በማሰናበት በግብ ጠባቂ አሰልጣኝ እየተመራ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካደረጋቸው 27 ጨዋታዎች አንዱን ብቻ በመርታት በ 9 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ 17 ጨዋታዎችን በመሸነፍ በደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቀምጧል። ጠንካራ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ቁጥሮች ሊደግፏቸው ያልቻሉት ኤሌክትሪኮች ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ሲያሳኩ ከለገጣፎ ለገዳዲ (19) በመቀጠል ሁለተኛውን ዝቀተኛ የግብ መጠን (23) በማስቆጠር እና ከለገጣፎ ለገዳዲ (59) በመቀጠል ሁለተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (46) ከድሬዳዋ ከተማ ዕኩል ማስተናገዳቸው ይህንን ሀሳብ ያረጋግጣል። ሆኖም ነገ የሚያደርጉት ጨዋታ ልዩነት የሚፈጥርላቸው ባይሆንም ለክብር በሚያደርጉት ግጥሚያ ከጫና ነጻ ሆነው በመቅረብ ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ።

\"\"

ከተከታታይ ሦስት የሽንፈት እና አራት የአቻ ውጤቶች በኋላ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በመቀመጫ ከተማቸው ባደረጉት የመጨረሻ ጨዋታ ወላይታ ድቻን 3-1 በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ኃይቆቹ ላሉበት የውጤት ማጣት ቀውስ ደግሞ ካለፉት 9 ጨዋታዎቹ በ 8ቱ ግቡን ያስደፈረው የተከላካይ መስመራቸው እንደ ምክንያት ይቆጠራል። ሆኖም ድል በተቀዳጁበት ሳምንት የታየው የሙጅብ ቃሲም እና የዓሊ ሱለይማን እንቅስቃሴ በሚፈለገው ደረጃ መገኘቱ የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ጫና የቀነሰ ነበር። አሰልጣኙ ከጨዋታው በኋላ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሦስት ዓይነት ሚና የሰጡትን ሙጅብ ቃሲምን ሁሉንም ኃላፊነቶች ተወጥቶ ለድል አብቅቶናል ብለው ያደነቁበት መንገድም ይህንን ይጠቁማል። ቡድኑ የነገውን ድል አሳክቶ ሦስት ደረጃዎችን አሻሽሎ 4ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥም ከኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚገጥመው ፈተና ቀላል አይሆንም።

በሀዋሳ ከተማ በኩል ብርሀኑ አሻሞ እና ወንድማገኝ ሀይሉ በጉዳት ጨዋታው የሚያልፋቸው ሲሆን መሐመድ ሙንታሪ ከቅጣት  ይመለሳል።

የነገው ጨዋታ በፕሪምየር ሊጉ 42ኛ ግንኙነታቸው ይሆናል። ባለፉት 41 ግንኙነቶች ኤሌክትሪክ 17 ሲያሸንፍ ሀዋሳ 14 አሸንፏል። 10 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።

– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የእርስ በእርሰ ግንኙነቶች ታሪክ 100 ጎሎችን የተሻገረ የመጀመርያው ግንኙነት የሆነው ይህ ፍልሚያ በ41 ጨዋታዎች 108 ጎሎች ሲቆጠሩበት ኤሌክትሪክ 62 ፣ ሀዋሳ 46 ጎሎችን አስቆጥረዋል።