የካፍ ኢንስትራክተሯ ኢትዮጵያዊት የላይቤሪያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት በርካታ ጉዳዮችን አጠናቃለች።
የላይቤሪያ ዜግነት ባላቸው ሮቨርት ላርቲ ይመራ የነበረው የሴቶች እግርኳስ ብሔራዊ ቡድን ኢትዮጵያዊቷን አሰልጣኝ ሰላም ዘርዓይን በምትኩ የሀገሪቷ የብሔራዊ ቡድን አለቃ አድርጎ ሊሾም ከጫፍ ስለ መድረሱ ታውቋል። የካፍ ኢንስትራክተር የሆነችው አሰልጣኝ ሰላም የቅዱስ ጊዮርጊስ ወጣት እና ዋና የሴቶች ቡድን እንዲሁም ደግሞ የኢትዮጵያ ታዳጊ እና ዋናው ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበረች ሲሆን በተጨማሪነት በያዝነው የውድድር ዓመት የአቃቂ ቃሊቲ የሴቶች ቡድንን ስታሰለጥን መቆየቷ ይታወሳል።
አሰልጣኟ በተለይ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠችው ሀሳብ የሀገሪቱን የሴቶች ብሔራዊ ቡድንን ለመያዝ ኮንትራት ለመፈረም አብዛኛው ሂደት ማለቁን እና የ20 ዓመት እና የ17 ዓመት በታች ቡድኖቹም መቆጣጠር በስምምነቱ ውስጥ እንደሚካተቱ ተናግራለች። አምስት ወራት በፈጀው የቅጥር ሂደት መነሻው ከላይቤሪያ እንደነበር እና ከሌሎች አሰልጣኞች ጋር በቃለ መጠይቅ ሂደት አልፋ አሁን ላይ የመጨረሻውን ኮንትራት ለመፈረም መቃረቧን ጨምራ ገልፃለች።