ከነገው ጨዋታ በፊት የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ምን አሉ ?

👉 \”…ጠንካራ ጨዋታ እንደሚገጥመኝ አምናለሁ ፤ ትልቅ ትንቅንቅ እና ትልቅ ትኩረት የሚፈልግ ጨዋታ ነው…\”

👉\” የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሁሌ የሚያደርጉትን ለክለቡ 12ኛ ተጫዋቾች ናቸው\”

የዘንድሮው ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ መጨረሻው እየተጠጋ ይገኛል። አሁን ላይ እየተከናወነ በሚገኘው 28ኛ ሳምንት መሀል ደግሞ ነገ ወሳኝ ጨዋታ ይደረጋል። ከ26ኛ ሳምንት በይደር የተያዘው ይህ ጨዋታ በመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በተከታዩ ባህር ዳር ከተማ መካከል የሚከናወን በመሆኑ ትልቅ ትኩረት ማግኘቱ አልቀረም። ይህንን ጨዋታ አስመልክተን ለቅዱስ ጊዮርጊሱ ዋና አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች እና የአሰልጣኙን ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበናል።

\"\"
እንደ አሰልጣኝ የነገውን ጨዋታ በምን ዓይነት ስሜት ነው የምትጠብቀው ?

\”ከባድ ጨዋታ ነው ግን ሁሉንም 15ቱንም ጨዋታ እንደምጠብቀው እና ለ15ቱም ቡድን እንደምዘጋጀው ነው እየተዘጋጀሁ ያለሁት።\”

የውድድር ዓመቱ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እንዴት ነው ?

\”በጣም ጥሩ የፍልሚያ መንፈሱ ከፍተኛ የነበረበት ነው። ይህ ዓመት በየክልሉ የሚደረገው ውድድር ከሜዳም ከዝናብም ጋር በተያያዘ በጣም ጠንካራ እና ከባድ የውድድር ዓመት ነው። ብዙዎቹ ቡድኖች ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ነበር። እንደቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ከፍተኛ ብቃት በማሳየት በሁሉም ጨዋታዎች ላይ ትኩረታችንን ከፍ በማድረግ ጥሩ ነገር ይዘናል። ይህ የውድድር ዘመን ጠንካራ ነው ብዬ ነው የማስበው።\”

የነገውን ጨዋታ እየጠበቁበት ስላለው ሁኔታ…

\”በዚህ ሰዓት እኛም ባህር ዳርም ሆነ ሌሎችም ጠንካራ ናቸው ብያለሁ። ከዚህ ውስጥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለው ባህር ዳር ነው እና ጠንካራ ጨዋታ እንደሚገጥመኝ አምናለሁ ፤ ትልቅ ትንቅንቅ እና ትልቅ ትኩረት የሚፈልግ ጨዋታ ነው። ጠንካራ ጨዋታ ስለሆነ ሁለታችንም ጥሩ ነገር የምናይ ይመስለኛል።\”

ስለ ተጋጣሚያቸው ባህር ዳር ከተማ…

\”ባህር ዳር ዘንድሮ የሚያሳየው እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነው። ያለበት ቦታም ይህንን ይገልጻል። ጥሩ ተጫዋቾችም አሉት። ዘንድሮ ባህር ዳር ያሳየው ጥንካሬ እና ያለው የቡድን ስብስብ በጣም ጥሩ ነው እና ባህር ዳር ከተማ በጣም በጣም ጥሩ ቡድን ነው።\”

ለነገው ጨዋታ በምን መልኩ እየተዘጋጃችሁ ነው ?

\”ምንም የተለየ ነገር የለውም ፤ ማንኛውም ቡድን እኛ ጋር ሲጫወት ጠንካራ እንቅስቃሴ እንደሚገጥመን አውቃለሁ። እያንዳንዱ ጨዋታችን ጠንካራ ነው እና አንዱ ደግሞ ነገ ከባህር ዳር የምናደርገው ጨዋታ ነው ፤ በአጠቃላይ በሁሉም የሜዳ ክፍል ላይ ጠንካራ ፉክክር ይኖራል።

\"\"

የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ከነገው ጨዋታ ምን ይጠብቁ ?

\”የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሁሌ የሚያደርጉትን ለክለቡ 12ኛ ተጫዋቾች ናቸው። የትም ብንገባ የሚደግፉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች አሉን እና አመለሸጋ እና ጥሩ ሥነምግባር ያላቸው ደጋፊዎች አሉን እና ነገም የተሻለውን ውጤት ለማምጣት ከተጫዋቾቹ ጋር አብረው ከጎን ሆነው ጥሩ ነገር እንድንሠራ ነው የምለው እንጂ ሁሌም የሚጠብቁት እና የምንዘጋጀው ለጥሩ ነገር ነው።\”