ከነገው ወሳኝ ጨዋታ በፊት የጣና ሞገዶቹ አሠልጣኝ ምን አሉ?

👉 \”ጨዋታው ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው\”

👉 \”…እንደየአመጣጡ ተገቢውን ግብረመልስ ለመስጠት በአካልም በአዕምሮም ዝግጁ ሆነን ጨዋታውን እየጠበቅን ነው\”

👉 \”በእንደዚህ ዓይነት ፍንዳታ ውስጥ ጓደኞቻቸውን በጉዳት ችግር ውስጥ ገብተው እያዩ ወደኋላ ሳያፈገፍጉ ሀዋሳ ድረስ ሲመጡ የተለየ ስሜት ነው የሚያጭረው ፤ …ታዲያ እነዚህን ደጋፊዎች ማስደሰት ከምንም በላይ ደስታን የሚፈጥር ነው\”

የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ሲቀጥሉ ነገ 10 ሰዓት በብዙሃኑ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቀው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ይደረጋል። ከጨዋታው አስቀድሞ የሁለቱ ቡድን አሠልጣኞችን ሀሳብ እያቀረብን ሲሆን አሁን ደግሞ የባህር ዳር ከተማን አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የቅድመ ጨዋታ አስተያየት እንደሚከተለው እናቀርባለን።

ብዙዎች የነገውን ጨዋታ በጉጉት እየጠበቁት ነው። አንተ እንደ አሠልጣኝ የነገውን ጨዋታ በምን አይነት ስሜት እየተጠባበክ ነው?

እንደሚታወቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ትልቅ ታሪክ ያለው ክለብ ነው። የሀገራችንም ቀደምት ክለብ ነው። በሊጉም በተደጋጋሚ ዋንጫ ያነሳ ትልቅ ታሪክ የፃፈ ክለብ ነው ነገ ተጋጣሚያችን ሆኖ የምናገኘው። ባህር ዳር ከተማም ወደ ሊጉ ከመጣ የአጭር ጊዜ ቆይታ ቢኖረውም ከጊዜ ጊዜ መሻሻሎችን እያሳየ የራሱን ቀለም እየያዘ በጠንካራ ተፎካካሪነት በተለይ በዘንድሮውን የውድድር ዓመት የተሻለ ፉክክር እያደረገ ይገኛል። ከዚህ አኳያ የነገው ጨዋታ ተጠባቂ ነው። አሁን ካለንበት ደረጃ እና ከያዝነው ነጥብ አኳያ ሲመዘን እንዲሁም ኳስ ወዳዱም ማኅበረሰብ እግርኳሱን ለማየት የሚፈልገው ጨዋታ ስለሆነ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው።

ጨዋታው ለእኛ ትልቅ ትርጉም አለው። አሸንፈን አሁን ያለውን የነጥብ ልዩነት አጥበን በፉክክር ውስጥ ለመቆየት ትልቅ ጉልበት ይሆነናል ፤ ቀሪ ጨዋታዎች እንዳሉን ታሳቢ ተደርጎ ማለት ነው። ስለዚህ ለእያንዳንዱ ጨዋታ የምንሰጠውን ግምት ለነገውም ጨዋታ ተገቢውን ግምት ሰጥተን ነው ወደ ሜዳ የምንገባው። በጥሩ ዝግጅት ላይ እንገኛለን። ተጫዋቾቻችን ላይ ያለው ተነሳሽነት እና የመጫወት ፍላጎት በመጣንበት መንገድ እያንዳንዱ ጨዋታ ላይ የታየ ስለሆነ ነገም በተሻለ ተነሳሽነት ወደ ሜዳ የምንመጣ ይሆናል። በዝግጅት ደረጃ በአጠቃላይ በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅተናል።
\"\"

የውድድር ዓመቱ ለባህር ዳር እንዴት እየሄደ ነው? ቀድሞ በነበራችሁ ዕቅድ ነው ዓመቱን እየተጓዛችሁ ያላችሁት?

ብዙ ፈታኝ ነገሮችን አልፈን እዚህ ደርሰናል። ተጫዋቾች የሚሰጣቸውን ነገር ለመስራት ያላቸው ተነሳሽነት እንዲሁም የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱ ጠዋት ማታ ሳይሰለች ቡድኑን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በትጋት መስራቱ እና ዕድለኛ የሚያደርገን ደግሞ የትልቅ ደጋፊ ባለቤት መሆናችን ጠቅሞናል። እንደሚታየው እግርኳስን የሚወድ ደጋፊ ነው ያለን። በየሄድንበት ከተማ እየተከተሉን ከጎናችን ነው ያሉት። እዛም ያሉት በያሉበት ቦታ በልባቸው ከእኛ ጋር ናቸው። አመራሩም በተቻለ አቅም እገዛዎችን እያደረገልን ነው እዚህ ደረጃ የደረስነው። የመጣንባቸው መንገዶች እንዲሁ አልጋ በአልጋ አልነበሩም። ውስጣዊው ውጫዊም ተግዳሮቶች ነበሩንና እነዛን በፅናት በመቋቋም ነው እዚህ የደረስነው። እንደምታየው ከሥነ-ምግባር ጋር ተያይዞ ተጫዋቾች ላይ ጠንካራ ሥራዎችን ለመስራት ሞክረናል። ቡድኑ ወጥ ሆኖ እንዲጓዝ መወሰን ያለብንን ውሳኔዎች ወስነን ነው እዚህ የደረስነው። እንደምታውቀው እነማውሊ ላይ የነበሩ ችግሮችን ጠንካራ ውሳኔ በመወሰን ነው እዚህ የደረስነው። ውጫዊ ተግዳሮቶችም ነበሩ። በተለይ ፍፁም በሚያስቆጭ መልኩ በሜዳ ላይ ነጥብ ያላገኘንባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። እነዛም ደግሞ ወደ ኋላ እንዳናፈገፍግ ሳያደርጉን የበለጠ ጉልበት ሆነውን እዚህ የደረስንበት ሁኔታ ነው ያለው። ሌላው ስንጀምር አካባቢ ብዙ የተጫዋቾች ጉዳቶች ያጋጥሙን ነበር። በአንድ ጨዋታ ከአራት እና ከአምስት ያላነሱ ተጫዋቾችን የምናጣበት ሁኔታም ነበር። እነዚህ እነዚህ በስራ እየተቀየሩ በአጠቃላይ በዓመቱ የመጣንበት ውድድር ጤናማ ነው ብዬ መናገር እችላለው። በእርግጥ የዓመቱ ውድድር አልተጠናቀቀም።

ስንነሳ የተነሳንበት መነሻ ሀሳብ አለ። በአስተማማኝ ደረጃ ከወራጅ ቀጠናው ነፃ ሆነን ቡድኑን በሊጉ የማቆየትና በቀጣይ ጠንካራውን ባህር ዳር ከተማ መገንባት የሚል ነበር የዓመት ዕቅድ ውስጥ አስገብተን ስራችንን የጀመርነው። እንዳየከው በአስተማማኝ ሁኔታ የምናደርገውን ጉዞ በመጀመሪያው ዙር ማጠናቀቂያ ነው እያረጋገጥን የመጣነው። እቅድ ተለዋዋጭ ነው። አሁን ላይ ደግሞ ሌላውን እንድናስብና የበለጠ እንድንጓዝ በመሆኑ አሁን ባለንበት ሁኔታ ፊታችን ላይ መልካም ነገሮች እንዳሉ ያሳያል። የተገኘውን ደግሞ አሟጠን ለመጠቀም ጠዋት ማታ እየሰራን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው። እንግዲህ ደጋፊዎቻችን ያላቸው ብርታት እስከ ምን ድረስ እንደሆነ በቅርብ ጊዜ የተከሰተው የቦንብ ጥቃት ትልቅ ማሳያ ነው ብዬ አስባለው። የደረሰባቸውን የቦንብ ጥቃት ተቋቁመው የተረፉ ልጆች ሀዋሳ ድረስ እኛን ለመደገፍ የነበራቸው ቁርጠኝነት የሚገርም ነው። እነዚህ እነዚህ ተጨማሪ ጉልበት ይሰጡሀል። ነገም የተሻለውን ውጤት አስመዝግበት እነዚህ ደጋፊዎቻችን እንዲደሰቱ የሁላችንም ምርጫነውና የምንችለውን ሁሉ ሜዳ ላይ እናደርጋለን ብዬ ነው የማስበው። እንደአጠቃላይ ደግሞ ቡድናችን የመጣበት መንገድ እጅግ አድካሚ እና ብዙ ስራዎችን የሚጠይቅ ቢሆንም ይሄንን በትጋት በመወጣታችን ነው እዚጋር ያለነው። ከፊታችን ያሉትን አራት ጨዋታዎች ደግሞ ውጤታማ ሆነን ለመጓዝ እስከመጨረሻው ያለንን አውጥተን በመጫወት በዓመቱ መጨረሻ የምንደርስበትን ደረጃ በፀጋ እንቀበላለን።

በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የነገው ጨዋታ ትልቅ ተፅዕኖ አለው። በጨዋታው ምን አይነት ፈተና ይገጥመናል ብለህ ታስባለህ?

ምናልባት እንደ አንድ ተግዳሮት ወይም ፈተና ይሆንብናል ብዬ የማስበው የተጫዋቾቻችን ተነሳሽነት ከልኩ እንዳያልፍ ነው። ምክንያቱም በጥሩ መንፈስ ላይ ነው ያሉት። ጨዋታውንም ማሸነፍ ይፈልጋሉ። እንደምትሰማው ደጋፊ እየተንቀሳቀሰ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ብዙ ደጋፊዎች በሜዳ ላይ ይገኛሉ። የበለጠ እነሱንም ለማስደሰት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ከልክ ያለፈ ፍላጎት እንዳይፈጠር ትንሽ ስጋት አሉኝ። በተረፈ ግን በእያንዳንዱ ጨዋታ ያላቸውን የመጨረሻውን ብቃት ለማውጣት ነው የሚጥሩት። ከተጋጣሚያችን ጋር ካለን የነጥብ ልዩነት አኳያና ከስሌት ደረጃ ምናልባትም ዘግቶ የመጫወት ወይም አቻውንም የመፈለግ ነገር ታሳቢ ያደርጋል ብለን እናስባለን። ከዚህ አንፃር እንደሚታወቀው የአዳማ ሜዳ በጣም ቆንጆ ሜዳ ነው። ምናልባት አሁን ያለው የአየር ፀባይ በዚሁ ይቀጥላል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገውና ከዚህ አኳያ ጥሩ ለመጫወት እንጥራለን። ከዚህ በተጨማሪም ሜዳ ላይ ጥሩ ዳኝነት እንዲኖር እንፈልጋለን። በጨዋታው ላይ ፍትሀዊ የሆነ ዳኝነት እንዲኖር እንፈልጋለን። ይሄም ይሆናል ብለን እናስባለን። ዳኞቻችን ከጨዋታ ጨዋታ ለውጦች እና እድገቶች እያሳዩ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። ስለዚህ የተሻለ ዳኝነት ይኖራል ብለን እናስባለን። እነዚህ ነገሮች ተሟልተው የምንጫወት ከሆነ ብዙ የምንቸገርበት ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም። በውድድር ግን በ90 ደቂቃ የሚፈጠረውን ነገር ከወዲሁ መገመት ቢከብድም የሚፈጠረውን አብረን የምናይ ይሆናል።

ጨዋታዎችን ሜዳ እየተገኘህ ትከታተላለህ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ የቅርብ ተፎካካሪህ ስለሆነ የቡድኑን እንቅስቃሴ በአንኩሮ እንደምታይ አስባለሁ። የነገ የተጋጣሚህን የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን እንዴት ትገመግመዋለህ?

በሜዳ ላይ ተገኝቶ ጨዋታዎችን መመልከት ሥራችንም ስለሆነ በቅርበት እያንዳንዱን እንቅስቃሴ መከታተል ግድ ይላል። እንደ ቡድን ሌሎችም አሰልጣኞች ተገኝተው ይመለከታሉ ብዬ ነው የማስበው። ነገም ቅዱስ ጊዮርጊስ ምን ዓይነት አቀራረብ ይዞ ይመጣል ለሚለው እኛ እነሱን እንደምንከታተል ሁሉ እነሱም የእኛን የጨዋታ መንገድ ይከታተላሉ ብለን እናስባለን። ከዚህ አኳያ እነሱም እኛ ከምናስበው በተቃራኒ መንገድ ሊመጡ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ። ሆኖም ግን እንደየአመጣጡ ተገቢውን ግብረመልስ ለመስጠት በአካልም በአዕምሮም ዝግጁ ሆነን ጨዋታውን እየጠበቅን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው። ከዛ በተረፈ ግን ከእነሱ የጨዋታ አቀራረብ አኳያ በአብዛኛው የምመለከተው በመስመር አጥቂዎቻቸውን የመጠቀም ፣ በቀጥተኛ ኳስ ደግሞ ትልቁን የጎል ምንጫቸውን አጎሮን ለማግኘት እሱን ዒላማ ያደረገ እንቅስቃሴ ይኖራቸዋል ብለን እንጠብቃለን። ካዛ በተረፈ ግን ፈጣን የመስመር አጥቂዎቻቸው በጥልቀትም ወደ ውስጥ እያስገቡ ለመጫወት የሚሞክሩበት ሁኔታ ይኖራል። በአብዛኛው ረጃጅም ኳሶችን በተለይ ወደ መስመር ያጋደሉ ኳሶችን ለመጠቀም ሲሞክሩ እናያለን። በአጠቃላይ እንደ ቡድን ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጫዋች ጥራት ደረጃም እንደ ቡድን የተሟላ ነው። ስለዚህ በተለያየ አቀራረብ ወደ ሜዳ የሚመጡበት አጋጣሚ ይኖራል ብዬ አስባለሁ። ለነገው ጨዋታ ደግሞ በምን መልኩ ይዘጋጃሉ የሚለውን የእነሱ የቤት ሥራ ነው የሚሆነው ፤ እኛ ግን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ሊጫወቱ ይችላሉ ብለን በምናስብበት መንገድ ይበልጥ የራሳችን እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ እና የእኛን የጨዋታ መንገድ ሳንለቅ ባሉን ልጆች ላይ ተመስርተን ዝግጅት እያደረግን ያለንበት ሁኔታ ነው ያለው። የነገው ጨዋታ ላይ ብዙ የተለየ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም ነገር ግን ለተመልካች አዝናኝ የሆነ የተሻለ እግርኳስ ይታያል ብዬ አስባለሁ።

\"\"
ጨዋታው ከመራዘሙ በፊት እናንተን ለመደገፍ ሊመጡ ሲሉ አደጋ የደረሰባቸው ደጋፊዎች ነበሩ። ስለእነሱ ምን ትላለህ? ብዙ ጊዜም ደጋፊዎችን ስታመሰግን ይሰማል። ከደጋፊዎቻችሁ ጋር ተያይዞ ያለህን ሀሳብ አጋራን?

ያው እንደሚታወቀው የባህር ዳር ከተማ ደጋፊ እጅግ በጣም ትልቅ ደጋፊ ነው ፤ ይህንንም የምለው በምክንያት ነው። አምና ካስታወስክ ቡድናችን አደጋ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ከተማው ላይ ምን ያህል ከጎናችን እንደነበሩ በዝናቡም በፀሐዩም ምንም ነገር ሳይበግራቸው ሁሌም ከቡድኑ ጎን እንደሆኑ ማንም የሚመሰክረው ነው። ደጋፊው እግርኳሱን ወድዶ ስፖርቱን ወድዶ የሚመጣ የተለየ ጥቅም የማያገኝ የተለየ ፍላጎት የሌለው ከምንም በላይ ግን ቡድኑን ወድዶ የሚደግፍ ደጋፊ ባለቤት ነን። ይህም በተግባር የታየ ነው ፤ ሰሞኑን የተከሰተውም ትልቅ ማሳያ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ፍንዳታ ውስጥ ጓደኞቻቸውን በጉዳት ችግር ውስጥ ገብተው እያዩ ወደኋላ ሳያፈገፍጉ ሀዋሳ ድረስ ሲመጡ የተለየ ስሜት ነው የሚያጭረው። ምን ያህል ክለባቸውን እንደሚወዱ ምን ያህል ለቡድናቸው ታማኝ እንደሆኑ ያየንበት ነው። ታዲያ እነዚህን ደጋፊዎች ማስደሰት ከምንም በላይ ደስታን የሚፈጥር ነው። እነዚህ ደጋፊዎች ተከፍሏቸው አይደለም እዚህ የሚመጡት ከኪሳቸው አውጥተው ነውና ብዙ ችግሮችን አልፈው ስለሚመጡ ያው የሁሉም ቡድን ደጋፊዎች ለቡድናቸው ፍቅር አላቸው ብዬ አስባለሁ ነገር ግን የእኛ ደጋፊዎች ይለያሉ ብዬ ብናገር ድፍረት አይሆንብኝም። አሁንም ወደፊትም ለደጋፊዎቻችን ትልቅ አክብሮት ነው ያለን። ለእኛ ጉልበት ናቸው ለእኛ ተጨማሪ ኃይል ናቸው። በእያንዳንዱ ጨዋታ ነገም ተጉዘው የሚመጡ ደጋፊዎቻችን አሉና እዚህ ብቻ አይደለም በያሉበት ቦታ ሆነው በ ዲኤስቲቪ የሚከታተሉ በሌላ አማራጮች በማህበራዊ ሚዲያ የሚከታተሉ ደጋፊዎች አሉንና ሁሉንም ባማከለ መልኩ ውጤታማ ሆነን ብናስደስታቸው የሁላችንም ምርጫ በመሆኑ ተጫዋቾቻችን በዚህ ደረጃ በትልቅ ተነሳሽነት ውስጥ ነው ያሉት እና ነገ በሚኖረን ጨዋታ የምንችለውን ሁሉ አድርገን የተሻለ ነገር እናስመዘግባለን የሚል ሀሳብ ነው ያለኝ ፤ ፈጣሪም ይጨመርበት የድካማችንን ውጤት የሚባርከው እርሱ ነውና። እስካሁንም በመጣንበት መንገድ የፈጣሪ እገዛ ታክሎበት በመሆኑ አሁንም በነገው ጨዋታ ላይ የተሻለ ነገር ለመሥራት ጥረት እናደርጋለን። እንደ አጠቃላይ ግን እስካሁን ለመጣንበት ጉዞ ደጋፊዎቻችን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉና በዚህ አጋጣሚ ደጋፊዎቻችንን ማመስገን እፈልጋለሁ።

ነገ ጨዋታውን የሚወስኑ የሜዳ ላይ ፍልሚያዎቹ ምን ቦታ ላይ ይበልጥ ይደረጋሉ ብለህ ታስባለህ?

በነገው ጨዋታ የመሃል ሜዳ ብልጫውን የሚወስድ ቡድን የተሻለውን ውጤት ያስመዘግባል ብዬ ነው የማስበው። ምክንያቱም ትልቅ የማጥቃት መነሻ የሚሆኑ ቁልፍ ቦታዎች እነዛ ስለሆኑ ከዚህ አኳያ በተሻለ መንገድ የተሻለ ነገር ለመሥራት ተዘጋጅተናል። በተረፈ ጨዋታው በመልካም ተጀምሮ በመልካም እንዲጠናቀቅ ምኞቴ ነው። ሁሉም የሚደሰትበት ጨዋታ እንዲሆን እመኛለሁ።