በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ 5ኛ ጨዋታ የተገናኙት ኢትዮጵያ እና ማላዊ ጨዋታቸውን ያለ ግብ ሲፈፅሙ ማላዊም ወደ አፍሪካ ዋንጫው የማለፍ ዕድሏን ሙሉ ለሙሉ አምክናለች።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጊዜያዊ አሠልጣኝ ዳንኤል ገብረማርያም በጨዋታው ሰዒድ ሀብታሙ፣ ሔኖን አዱኛ፣ አስቻለው ታመነ፣ ያሬድ ባየ፣ ረመዳን የሱፍ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ፣ ሀብታሙ ታደሠ እና ቢኒያም በላይን በቀዳሚ አሰላለፋቸው አካተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ ያስተናገደው በ12ኛው ደቂቃ ነው። በዚህም ቻዋናንጉዋ ካዎንጋ በቀኝ የሳጥኑ ክፍል ተገኝቶ የሞከረውን ኳስ የግብ ዘቡ ሰዒድ ሀብታሙ በጥሩ ቅልጥፍና አድኖታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ዋልያዎቹ በጥሩ የኳስ ቅብብል ማላዊ ሳጥን ደርሰው አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ቢወጥኑም ከነዓን የመታውን የመጨረሻ ኳስ ተከላካዮች አውጥተውታል።
በተለይ በቀኝ መስመር በኩል ትኩረት ሰጥተው ለማጥቃት የሚጥሩት ነበልባኖሎ ከቅጣት ምት እና ከመዓዘን ምትም የግብ ምንጭ ለማግኘት ሞክረዋል። በተለይ በ27ኛው ደቂቃ ዴኒስ ቺምቤዚ ከመዓዘን ምት መነሻን ያደረገ ኳስ ቅርቡ ቋሚ ጋር በማግኘት ያደረገው የግንባር ሙከራ እጅግ ለግብ የቀረበ ነበር። በተቃራኒው በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ እጅግ ብልጫ የወሰዱት ዋልያዎቹ በማጥቃቱ ላይ ውስንነቶች ቢኖሩትም ጨዋታውን በመቆጣጠሩ ረገድ የተሻለ ነበር።
36ኛው ደቂቃ ላይ የማላዊው የቀኝ መስመር ተከላካይ ሳኑዲ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ቻዋናንጉዋ ካኦንጋ ያደረገውን ሙከራ ያሬድ ባዬህ ተደርቦ ሲያስወጣበት በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ኢዳኒ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ሰዒድ ሀብታሙ መልሶበታል። ለዕረፍት ሊያመሩ ሴኮንዶች ሲቀሩ ደግሞ ምዋሴ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት በተሻገረለት ኳስ በግንባሩ በመግጨት ጥሩ ሙከራ አድርጎ ሰዒድ ሀብታሙ አምክኖበታል።
በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ የወጡት ዋልያዎቹ በ55ኛው ደቂቃ መሪ የሚሆኑበትን ዕድል ፈጥረው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ቢኒያም በላይ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ ቆሞ የነበረው ከነዓን ማርክነህ አግኝቶት በአንድ ንክኪ ወደ ግብ ቢመታውም ግብ ጠባቂው መልሶበታል።
በዚህኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተከላክሎ መጫወትን ምርጫቸው ያደረጉት ማላዊዎች አጨዋወታቸው የኢትዮጵያ የማጥቃት አጨዋወት በመጠኑ ያነቃቃ ነበር። አሠልጣኝ ዳንኤልም የማላዊን አጨዋወት በማየት የማጥቃት ኃይላቸው ላይ ለውጥ በማድረግ ግብ ፍለጋቸውን ተያይዘዋል። በ71ኛው ደቂቃም ዱሬሳ ሹቢሳን ተክቶ የገባው ዮሴፍ ታረቀኝ ጥሩ ሙከራ ሰንዝሯል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቢኒያም በተቃራኒ አቅጣጫ ሌላ ዕድል ፈጥሮ በግብ ዘቡ መክኗል። ቀሪ ደቂቃዎች ሌላ ዕድል ሳይፈጠርበት ጨዋታው አቻ ተጠናቋል።
በምድቡ ግብፅ ቀድማ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ማለፏን ማረጋገጧ የሚታወስ ሲሆን ይህ ጨዋታ በአቻ ውጤት መፈፀሙን ተከትሎ ጊኒ ግብፅን ተከትላ ማለፏን ያረጋገጠች ሌላኛዋ ሀገር ሆናለች። በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታ በነሐሴ ወር መጨረሻ ኢትዮጵያ ከግብፅ ማላዊ ደግሞ ከጊኒ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።