በምሽቱ ጨዋታ ሲዳማ ቡና ባህር ዳር ከተማን 4-0 በመርታት ለከርሞው በሊጉ ለመቆየት ራሱን አደላድሏል።
በተነቃቃ እንቅስቃሴ የጀመረው ጨዋታ አልፎ አልፎ ወደ ሁለቱም ግቦች የሚሰነዘሩ ፈጠን ያሉ ጥቃቶች እና ለግብ ሙከራነት የቀረቡ ሂደቶችን እያሳየን ቆይቶ 19ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ተስተናግዶበታል። ከመሀል ሜዳ የተሻገረን ኳስ ፋሲል ገብረሚካኤል በአግባቡ ሳይርቀው ቀርቶ ያገኘው ፍሬው ሰለሞን ከመረብ አገናኝቶታል። ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም አበባየሁ ዮሐንስ ከሲዳማ ሜዳ በረጅሙ የላከውን ኳስ ፍሊፕ አጃህ ሳጥን ውስጥ ይዞ በመግባት እና ተስፋዬ ታምራትን በአንድ ለአንድ ግንኙነት በማሸነፍ የሲዳማ ቡናን መሪነት ወደ ሁለት ያሳደገች ጎል አስቆጥሯል።
በጊዜ ለመመራት የተገደዱት ባህር ዳሮች በቀጣይ ደቂቃዎች በንፅፅር በተሻለ ሁኔታ ወደ ጨዋታው ለመመለስ በተለይም ወደ ግራ አድልተው ተንቀሳቅሰዋል። 35ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሰ ከቀኝ የእጅ ውርወራ ይዞ በመግባት ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረገበት እንዲሁም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ፍፁም ጥላሁን ከቅጣት ምት የሞከረበት ቅፅበት ቡድኑ በተሻለ ሁኔታ ወደ ግብ የቀረበባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ሲዳማዎችም በመልሶ ማጥቃት ምላሽ ለመስጠት የሞከሩ ሲሆን በተለይም አጋማሹ ሊገባደድ ሲል ፍሊፕ አጃህ እና አበባየሁ ዮሐንስ ልዩነቱን ለማስፋት ተቃርበው ነበር።
ከዕረፍት መልስ የጣና ሞገዶቹ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም ከኋላ የሚተዉት ሰፊ ክፍተት ለሲዳማ የመልሶ ጥቃት ምቹ ሲያደርጋቸው ታይቷል።
ከዚህ መሀል በቀዳሚነት 53ኛው ደቂቃ ላይ ፍሊፕ አጃህ ሳጥን ውስጥ ደርሶ መትቶት ሀብታሙ ታደሰ ወደ ኋላ ተስቦ በሸርተቴ ያወጣበት ሙከራ ይጠቀሳል። በባህር ዳር በኩል ደግሞ 59ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነ ከፍሬው ያስጣለውን ኳስ ከሳጥን ውጪ በመምታት ያደረገው ጠንካራ ሙከራ በፍሊፕ ኦቮኖ ጥረት የዳነ ነበር።
ሲዳማዎች በቶሎ ከሜዳቸው ወጥተው የሚሰነዝሯቸው ጥቃቶች 74ኛው ደቂቃ ላይ ከውጤት አድርሷቸዋል። ተቀይሮ የገባው ሳላዲን ሰዒድ የጨዋታው ኮከብ ከነበረው ፍሬው ሰለሞን ጋር ባደረገው ቅብብል ወደ ባህር ዳር ግብ ቀርቦ አለልኝን በማታለል ሦስተኛ ግብ አስቆጥሯል። ከግቡ ሁለት ደቂቃዎች በኋላ አለልኝ አዘነ በክርን ተማቷል በሚል በዕለቱ አርቢትር ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል።
ሳላዲን ሰዒድ ካመከነው ሌላ ያለቀለት የግብ ዕድል በተረፉት ባህር ዳር ከተማዎች ደካማ የማጥቃት ጥረት የቀጠለው ጨዋታ በጭማሪ ደቂቃ ለሲዳማ ፌሽታ የሆነ አራተኛ ጎል ተቆጥሮበታል። የመጀመሪያው ጎል መንትያ በሆነ አጋጣሚ የፋሲልን ኳስ የማራቅ ስህተት ተጠቅሞ ፍሬው ሰለሞን በደጋሚ በግብ ጠባቂው አናት ላይ በመላክ ጨዋታውን በጎል አሳርጓል። በውጤቱ ባህር ዳር ከተማ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በስድስት ነጥቦች ለመራቅ ሲገደድ ጣፋጭ ድል ያሳካው ሲዳማ ቡና በበኩሉ የወራጅ ቀጠናውን በአምስት ነጥቦች መራቅ ችሏል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቡድናቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴ እንደከዚህ ቀደሙ እንዳልነበር ያመኑት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በዚህ ልክ መሸነፍ እንዳልነበረባቸው ጠቁመዋል። ቀጥለውም ተጋጣሚያቸው በተነሳሽነት የነበረውን ብልጫ አድንቀው እንደቡድን ለተፈጠረው ውጤት ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በበኩላቸው ከሀዋሳው ውድድር ጀምሮ ስለተመለሰው የአሸናፊነት መንፈሳቸው አብራርተው ውጤቱ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ባህር ዳር ከተማ እንደቀደመ ብቃቱ ሆኖ እንዳላገኙት የጠቆሙ ሲሆን ፍሬው ሰለሞን ሊያሻሽል ስለሚገባቸው ነጥቦች አንስተው በዛሬው ውጤት ከስጋቱ የተሻለ ደረጃ ላይ መገኝት እንደቻሉ ተናግረዋል።