ቡናማዎቹ አዲስ የውጭ ሀገር አሰልጣኝ ወደ ኢትዮጵያ አምጥተዋል

ሶከር ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባጋራቻችሁ መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ቡና የውጭ ሀገር ዜግነት ያለው አሰልጣኝ መሾሙ እርግጥ ሆኗል።
\"\"
የያዝነው የውድድር ዓመት እንዳሰቡት ያልሆነላቸው ቡናማዎቹ ለ2016 የውድድር ዘመን ራሳቸውን በተሻለ ተፎካካሪ አድርገው ለመቅረብ ከሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ይልቅ የውጭ ሀገር አሰልጣኝ ለመሾም እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ዘግበን ነበር። የኢትዮጵያ ቡና ስራ አመራር ቦርድ የተለያዩ የውጭ አሰልጣኞችን የስራ ልምድ ከመረመመረ በኋላ በስተመጨረሻም አሰልጣኝ መሾሙ ታውቋል።

አዲሱ የቡና አሰልጣኝ ሰርቢያዊው ኒኮላ ካቫዞቪች ይባላሉ። የ47 ዓመቱ ሰርቢያዊ ከዚህ ቀደም በታጃኪስታን፣ ሲሪ ላንካ እና ባንግላዲሽ ሊጎች ያሰለጠኑ ሲሆን ወደ አህጉራችን አፍሪካም መጥተው በቦትስዋና ታውንሺፕ ሮለርስን፣ በደቡብ አፍሪካ ፍሪ ስቴት ስታርስን እንዲሁም በኬኒያ ሊዩፓርድስን መርተዋል።

\"\"
አሠልጣኙ ባሳለፍነው ሳምንት በአቻ ውጤት የተጠናቀቀውን የሸገር ደርቢ ጨዋታ ከክለቡ ፕሬዝደንት እና ስራ አስኪያጅ ጋር በመሆን በስታዲየም በመገኘት የታደሙ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በልምምድ ሜዳ በመገኘት ቡድኑን እየተመለከቱ እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። የውል ዘመናቸው ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ በግልፅ መረጃዎች ባይወጡም በቅርቡ ዝርዝር ጉዳዮች በጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።