ከሀገሪቷ ትልቁ የሊግ ዕርከን ከወር በፊት መሰናበቱ የተረጋገጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ለቀጣዩ ዓመት የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎው አዲስ አሰልጣኝ በዛሬው ዕለት ሾሟል።
2010 ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከወረደ በኋላ በያዝነው የውድድር ዓመት በድጋሚ ተመልሶ ሲወዳደር የሰነበተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ የዘንድሮውን የውድድር ዘመን በአሳዳጊ አሰልጣኙ ክፍሌ ቦልተና መሪነት ሊጉን ቢጀምርም የኋላ ኋላ በውጤት መጥፋት የተነሳ ከአሰልጣኙ ጋር በመለያየት በቀሩት ጊዜያት በሦስት የተለያዩ አሰልጣኞች ሲመራ ቆይቷል።
ሆኖም በመጣበት ዓመት ከፕሪምየር ሊጉ በጊዜ መውረዱ የተረጋገጠ ሲሆን ቀጣዩን ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ለሚያደርገው ጉዞ ከወዲሁ እንቅስቃሴዎችን በመጀመር ቀዳሚው ተግባሩ አዲስ አሰልጣኝ መሾምን አድርጓል። በዚህም መሠረት አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን ክለቡ ለቀጣዩ አንድ ዓመት በዋና አሰልጣኝነት በዛሬው ዕለት መሾሙን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ የላከው መረጃ ያመላክታል።
አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም በሐረር ቢራ ፣ ዳሽን ቢራ ፣ ስሑል ሽረ እና ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማን ተረከበው ሲያሰለጥኑ መቆየታቸው ይታወሳል።