ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሀያ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ መደረግ ይቀጥላሉ። በነገው ዕለት የሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ !
ሀድያ ሆሳዕና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ለ29ኛ የሊግ ክብራቸው በእጅጉ የቀረቡት ፈረሰኞቹ እና ነብሮቹ የሚያደርጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነገ 09:00 ላይ ይከናወናል።
በአርባ ነጥቦች በሰባተኛ ደረጃነት የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ይሄንን ጨዋታ ማሸነፍ ወደ አራተኛ ደረጃነት ስለሚያሸጋግራቸው በዚህ ወሳኝ እና ተጠባቂ ጨዋታ ነጥብ ለማግኘት አልመው እንደሚገቡ እሙን ነው።
ነብሮቹ ወጥነት የሌለው ብቃት በማሳየት ላይ ይገኛሉ። በሀያ አራተኛው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር አቻ ከተለያዩ በኋላ ሳይጠበቅ ጠንካራውን ባህርዳር ከተማ ቢያሸንፉም ከዚያ በኋላ ኳደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ዘጠኝ ነጥቦች አራቱን ብቻ አሳክተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪክን አሸንፈው በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ገጥሟቸው ከአዳማ ጋር አቻ ተለያይተዋል።
በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ባዶ ለባዶ አቻ ተለያይተው፤ ግብ የማስቆጠር ችግር ታይቶባቸው የነበሩት ነብሮቹ ከዛ በኋላ ግን ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች አስቆጥረዋል። ይህ ማለት በአማካይ በጨዋታ ሁለት ግቦች ነው። ይህ ቁጥር እንደሚያመለክተውም ቡድኑ በዚህ ወቅት ምን ያህል ጠንካራ የማጥቃት ክፍል እንዳለው ነው። ይህንን ጠንካራ ጎን ማስቀጠል የሚችሉ ከሆነ ደግሞ ለፈረሰኞቹ የተከላካይ ክፍል ፈተና መሆናቸው አይቀሪ ነው። ሆኖም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው ከተጋጣሚያቸው የማጥቃት ጥንካሬ እና ጥራት አንፃር ሲታይ ከባድ ፈተና እንደሚጠብቃቸው የታወቀ ነው። አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹም ይህንን የቡድኑ ችግር በነገው ጨዋታው የማስተካከል ትልቅ ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል።
በፈረሰኞቹ ለዚህ ጨዋታ በሜዳው ከሜዳም ውጪ የተለየ ትኩረት ሰጥተው እንደሚገቡ ለመገመት አያዳግትም። ለምን ቢባል ከነገው ጨዋታ ነጥብ ካገኙ 29ኛ የሻምፕዮንነት ካባቸው የሚደርቡት ልዩ ቀናቸው ስለሆነ ነው።
በስልሳ ነጥቦች በሊጉ አናት ላይ ተቀምጠው ተከታያቸውን በስድስት ነጥቦች ልዩነት የሚመሩት ፈረሰኞቹ ምንም እንኳ በተከታታይ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ስድስት ነጥቦች ሁለቱም ብቻ ቢያሳኩም የነገው ጨዋታ ካለው ወሳኝነት አንፃር የተለየ አቀራረብ ይዘው በመቅረብ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዘው ለመውጣት አልመው እንደሚገቡ ይታመናል።
ጊዮርጊሶች በርካታ የግብ ምንጭ ያለው ጠንካራ የሚባል የማጥቃት ክፍል አላቸው። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ያስቆጠርዋቸው ስምንት ግቦችም ለዚህማሳያ ናቸው። ተጋጣምያቸው በወቅታዊነት ካለው መጥፎ የመከላከል ክብረ ወሰን አንፃር ስናየውም በዛ ረገድ ይቸገራሉ ተብሎ አይገመትም። ሆኖም ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ ያልወጣው እና ስምንት ግቦች የተቆጠሩበት (በአማካይ በጨዋታ 1.1 ግብ) የተከላካይ ክፍላቸው ጥገና ሳያስፈገው አይቀርም። ለምን ቢባል ተጋጣሚው ሀድያ ሆሳዕና መጨረሻ ካደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስመዘገበ ጠንካራ የማጥቃት ክፍል ባለቤት ስለሆነ ነው።
ከቡድን ዜና ጋር በተያያዘ የነብሮቹ ሪችሞንድ ኦዶንጎ ፣ ስቴፈን ኒያርኮ፣ መሳይ አያኖ ፣ እንዳለ ደባልቄ እና አክሊሉ ዋለልኝ ከቡድናቸው ጋር አይገኙም። ቤዛ መድህንና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ደግሞ በጉዳትና በቅጣት ክለባቸው የማያገለግሉ ተጫዋቾች ናቸው። ፈረሰኞቹ በጉዳትም ቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ በስሰባት ጨዋታዎች የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሦስት ጊዜ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ሲችሉ የተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ በመጋራት የተጠናቀቁ ነበሩ።
ባህር ዳር ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
ደረጃውን የማሻሻል ዕድል ያለው ሀዋሳ ከተማ እና የተሟጠጠ የዋንጫ ተስፋ ያለው ባህርዳር ከተማ የሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ የሳምንቱ ማሳረጊያ ይሆናል።
በአርባ አንድ ነጥቦች በአምስተኛ ደረጃነት የተቀመጡት ሀዋሳዎች ይህንን ጨዋታ ካሸነፉ ደረጃቸው ያሻሽላሉ። ይህንን ተከትሎም ለጨዋታው ትልቅ ትኩረት ሰጥተው እንደሚገቡ ይገመታል።
ሀዋሳዎች መጨረሻ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ኤሌክትሪክና ወላይታ ድቻን አሸንፈው በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ይገኛሉ። በነገው ጨዋታም በተጠቀሱት ጨዋታዎች ጥሩ የነበረው እና አምስት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸው እና ጥሩ ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው የተረጋጋው የተከላካይ ክፍላቸው በተመሳሳይ ጥንካውን ማስቀጠል ከቻሉ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ይቸገራሉ ተብሎ አይገመትም።
ሀዋሳ ከተማ እንደ ሌሎች የሊጉ ክለቦች የወጥነት ችግር አለበት። ቡድኑ በሲዳማ ቡና የአንድ ለባዶ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሽንፈት ባይገጥመውም በተከታታይ አራት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ ነጥቦች ለመጣል ተገዷል። ይህ ማለት በጨዋታዎቹ ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥቦች አራት ብቻ ነው ማሳካት የቻለው።
በፕሪምየር ሊግ ታሪካቸው አስደናቂውን ዓመት በማሳለፍ የሚገኙት የጣና ሞገዶች ከተቻለ እስከ መጨረሻው ሳምንት ድረስ ታግለው ያላቸውን የተሟጠጠ የዋንጫ ዕድል ለማሳካት እንደሚጫወቱ እሙን ነው።
በአሰልጣኝ ደግአረገ ስር በአመዛኙ በፈጣን ሽግግር ላይ ተመስርተው ጥሩ ዓመት ያሳለፉት ባህር ዳሮች በመጨረሻዎቹ አራት ሳምንታት የውጤት መዋዠቅ ገጥሟቸው ከዋንጫ ፉክክሩ እንዲርቁ ሆኗል። በተጠቀሱት አራት ጨዋታዎች አንድ ድል፣ አንድ አቻ እና ሁለት ሽንፈት ገጥሟቸዋል። በጨዋታዎቹም ከውጤት ቀውሱ ባልተናነሰ ትኩረት የሚስበው የነበራቸው ደካማ የመከላከል አደረጃጀት ነው። በአራቱ ጨዋታዎችም አስር ግቦች አስተናግደዋል፤ በጨዋታ በአማካይ 2.4።
በነገው ጨዋታ ግን ይህንን መጥፎ ክብረ ወሰን መግታት ይጠበቅባቸዋል። የተከላካይ ክፍሉም ከሌሎች የቡድኑ ክፍሎች በበለጠ መጠነኛ ጥገና ይሻል። የነገው ተጋጣሚው በሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረው ሀዋሳ ከተማ መሆኑ ሲታይ ደግሞ ጉዳዩ አንገብጋቢ ያደርገዋል።
ሀዋሳዎች አሁንም የብርሀኑ አሻሞ እና ወንድማገኝ ሐይሉ ግልጋሎት አያገኙም። ባህር ዳር ከተማዎችም አማካያቸው አለልኝ አዘነ በቅጣት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያሰልፉም።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ ቀባት ጊዜ ተገናኝተው ሦስቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ሀዋሳ ሦስቴ ባህር ዳር ደግሞ አንድ ጊዜ ድል አድርገዋል።