የ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ የሆነው የድሬዳዋ ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ1-1 ተጠናቋል።
9 ሰዓት ላይ የ 2015 ዓ.ም የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሲያገናኝ ቻምፒዮንነቱን ያረጋገጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ የክብር አቀባበል ሲደረግለት የውድድሩ ዋንጫ ደግሞ በክለቡ ታሪካዊ ተጫዋች ደጉ ደበበ አምባሳደርነት ወደ ሜዳ ወጥቷል።
አምስት ደቂቃዎች ያህል ዘግይቶ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በታዳጊ ተጫዋቾች የገቡት እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ፈረሠኞቹ ከተከላካይ ጀርባ በሚተውት ቦታ በድሬዳዋ ከተማ አጥቂዎች በተለይም በሙኸዲን ሙሳ በመጠኑ ሲፈተኑ ተስተውሏል። ሆኖም የመስመር አጥቂው ሙኸዲን ሙሳ 9ኛው ደቂቃ ላይ ሱለይማን ሃሚድን አታልሎ በማለፍ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ተመስገን ዮሐንስ አስወጥቶበታል። ይህም የጨዋታው የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር።
በሚያገኙት ኳስ ሁሉ በጥቂት ንክኪዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ያልተቸገሩት ብርቱካናማዎቹ 30ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በውድድር ዓመቱ የክለቡ የመጀመሪያ እና የሊጉ ደግሞ ሦስተኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ቢኒያም ጌታቸው ከመሃል ሜዳ በተሻገረለት ኳስ ግብ ጠባቂውን ተመስገን ዮሐንስን በቀላሉ በማለፍ አስቆጥሮታል። ግቡም ለአጥቂው 14ኛ ግቡ ሆና ተመዝግባለች።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ጊዮርጊሶች የመጀመሪያውን የጠራ የግብ ዕድላቸውን 38ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ በቀኝ መስመር ከማዕዘን የተነሳውን ኳስ ያገኘው አላዛር ሳሙኤል ያደረገውን ሙከራ በትክክለኛ ቦታ ላይ የነበረው የመሃል ተከላካዩ አሳንቴ ጎድፍሬድ ተደርቦ አግዶበታል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስት ያህል ደቂቃዎች ሲቀሩ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወርቃማ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ተገኝተው ነበር። በቅድሚያም 42ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው ቢኒያም ጌታቸው ከ ብሩክ ታረቀኝ የቀማውን ኳስ ከረጅም ርቀት እየገፋ በመሄድ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም በወረደ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ሲቀር በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ 45+1\’ ላይ አላዛር ሳሙኤል ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ያደረገውን ሙከራ የድሬው ግብ ጠባቂ ፍሬው ጌታሁን በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበታል።
ከዕረፍት መልስ ድሬዳዋ ከተማዎች ተቀዛቅዘው ሲቀርቡ ጊዮርጊሶች በአንጻሩ በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመግባቱ በኩል ብልጫውን መውሰድ ችለዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይም ሱለይማን ሃሚድ ከቅጣት ምት ያደረገውን ፈታኝ ያልሆነ ሙከራ ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን መልሶበታል።
ፈረሠኞቹ 55ኛው ደቂቃ ላይ የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እስማኤል ኦሮ አጎሮ እና ቢኒያም በላይን ቀይረው ሲያስገቡ የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቅያሪ በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ውጤታማ አድርጓቸዋል። ቢኒያም በላይ ያቀበለውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት የገባው ዳግማዊ አርዓያ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው በረከት ወልዴ ወደ ግብነት ቀይሮት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላም ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሄዶ ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግበት 1-1 ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ከዋንጫ ርቀው በመቆየታቸው እና በሁለት ዓመታት የተደረጉ 60 ጨዋታዎችን ከከተማ ውጪ በማድረጋቸው እና በእነዚህ ዓመታትም ተከታታይ ዋንጫ ማንሳታቸው የተለየ ደስታን እንደፈጠረባቸው በመግለጽ እና በቻምፒየንስ ሊግ የተሻለ ጊዮርጊስ ለማሳየት ያላቸውን ሁሉ ለማድረግ እንደሚሞክሩ ሲናገሩ ለዚህ ስኬታቸው እንዲበቁ የደገፏቸውን አካላት አመስግነዋል። የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ አሥራት አባተ በበኩላቸው ጨዋታው ጠንካራ እንደነበር በመግለጽ ተጫዋቾቻቸው ከቻምፒዮኑ ቡድን ልምድ አግኝተው ሄደዋል ብለው እንደሚያምኑ እና በሁሉም ጨዋታዎች ድክመታቸውን ጠንቅቀው እንዳወቁ ሲናገሩ ለቀጣይ አሻሽለው በመምጣት ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።