የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቁልፍ ውሳኔዎች አሳልፏል

በኢትዮጵያ ዋንጫ ፣ በፕሪምየር ሊግ ወራጆች ቁጥር እና በትግራይ ክልል ክለቦች መመለስ ዙሪያ አዳዲስ ውሳኔዎች ተሰምተዋል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ በእግርኳሱ ከባቢ ትልልቅ የሚባሉ ጉዳዮችን ተመልክቶ በቀጣዩ የውድድር ዓመት ልዩነት የሚፈጥሩ ውሳኔዎች ላይ መድረሱን በማህበራዊ ገፆቹ ይፋ አድርጓል።

\"\"

ከእነዚህ መካከል ቀዳሚው የኢትዮጵያ ዋንጫን የተመለከተ ነው። ከ1937 ጀምሮ ይከናወን የነበረው በቀድሞው አጠራሩ \’የኢትዮጵያ ጥሎማለፍ ዋንጫ\’ ውድድር በተለያዩ ጊዜያት ሲቋረጥ እና ሲቀጥል የነበረ መሆኑ ይታወሳል። በመጨረሻዎቹ ዓመታት \’የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የጥሎማለፍ ዋንጫ\’ በሚል ስያሜ ሲከናወን ለመጨረሻ ጊዜ 2011 ላይ በፋሲል ከነማ አሸናፊነት ተጠናቆም ነበር። ምንም እንኳን የውድድሩ አሸናፊ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ይወክል የነበረ ቢሆንም ከተቋረጠ በኋላ ግን በፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛ ሆኖ በሚጨርስ ቡድን ለመተካት ተገዶ ቆይቷል ። ፌዴሬሽኑ ይህንን አካሄድ ወደነበረበት መልሶ ውድድሩ ማሻሻያ ተደርጎበት \’የኢትዮጵያ ዋንጫ\’ በሚል መጠሪያ የፕሪምየር ሊግ እና ከፍተኛ ሊግ ክለቦችን በማሳተፍ በ2016 የውድድር ዓመት ዳግም እንደሚመለስ አስታውቋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የውድድሩ አሸናፊ ወደ አፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ እንደሚያመራም ታውቋል።

ሁለተኛው ጉዳይ ከፕሪምየር ሊጉ የሚወርዱ እና ከከፍተኛ ሊጉ የሚያድጉ ክለቦችን ቁጥር የተመለከተ ነው። ፌዴሬሽኑ በተለይ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ኢትዮጵያ ኘሪሚየር ሊግ የሚያድጉ ክለቦች በውድድር አቅም እና በአደረጃጀት የተሻሉ እና ተፎካካሪ መሆን እንዳለባቸው ከግምት አስገብቶ በቀጣዩ ዓመት አዲስ አስራር እንደሚተገብር ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ከፕሪምየር ሊጉ የሚወርዱ እና ከከፍተኛ ሊጉ የሚተኳቸው ክለቦች ቁጥር በቀንድ ቀንሶ ሁለት እንዲሆን ከውሳኔ ላይ ተደርሷል። በዚህም መሰረት ከ2007 የውድድር ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2016 ሁለት ክለቦች ወደ ፕሪምየር ሊጉ አድገው ሁለት ክለቦች ደግሞ የሚወርዱ ይሆናል።

ሦስተኛው ውሳኔ የትግራይ ክልል ክለቦችን የተመለከተ ነው። በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በነበረው ጦርነት ምክንያት ከ2012 በኋላ ከውድድር ርቀው የቆዩት የትግርይ ክልል ክለቦች ወደ ውድድር ለመመለስ እንቅስቃሴ እንደጀመሩ ይታወቃል። ዛሬ ፌዴሬሽኑ የክልሉን ክለቦች ዕጣ ፈንታ አስመልክቶ በደረሰበት መደምደሚያ መሰረት ደግሞ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ክለቦቹ ወደ ውድድር እንደሚመለሱ ታውቋል። ክለቦቹ በሚመለሱበት አግባብ ዙሪያ ፌዴሬሽኑ በወሰነው ውሳኔ መሰረት ቀደም ሲል ከነበሩበት የሊግ ዕርከን በአንድ ዝቅ ብለው ወደ እግርኳስ ውድድሮች ተሳትፎ ይመለሳሉ። በዚህም መሰረት በኘሪሚየር ሊግ ሲወዳደሩ የነበሩ ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊግ ፣ በከፍተኛ ሊግ ይወዳደሩ የነበሩ ክለቦች ወደ አንደኛ ሊግ እንዲሁም በአንደኛ ሊግ ሲወዳደሩ የነበሩ ክለቦች ወደ ትግራይ ክልል የሊግ ውድድር ዝቅ ብለው 2016 ላይ ወደ እግርኳሱ መድረክ እንዲመለሱ መወሰኑ ይፋ ሆኗል።

\"\"